ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሱዳን ጦር በርካታ አካባቢዎን ጥሎ ለመውጣት ተገዷል።
የምስሉ መግለጫ,ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሱዳን ጦር በርካታ አካባቢዎን ጥሎ ለመውጣት ተገዷል።

18 ህዳር 2023, 08:31 EAT

በሱዳን ዳርፉ ግዛት የሚንቀሳቀሱ ሁለት አማጺ ቡድኖች ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጎን ተሰልፈን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አሳወቁ።

ሁለቱ አማጺ ቡድኖች ይህን ያሉት ከአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ወታደራዊ ድሎችን እያስመዘገበ ባለበት ወቅት ነው።

ከአገሪቱ ጦር ጎን ሆነን የጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎን ጦር ለመውጋት ዝግጁ ነን ያሉት የፍትሕ እና እኩልነት ንቅናቄ (ጄም) እና የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ (ኤስኤልኤም) አማጺ ቡድኖች ናቸው።

የጄም መሪ የሆኑት ጅብሪል ኢብራሂም ሠራዊታቸው ከጦሩ ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት የወሰነው ሰዎችን በሕይወት እያሉ ከሚቀብረው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል “ሰላማዊ ሕዝባችንን መከላከል ስላለብን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአማጺው ቡድን መሪ በአንድ ወቅት ሲዋጋው ከነበረው ከአገሪቱ ጦር ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት ከውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል እንዳልነበር ተናግረዋል።

ጄም እና የሱዳን ጦር መልካም ግንኙነት የላቸውም። በአንድ ወቅት በጠላትነት ተፈራርጀው ጦር ተማዘዋል። የጅብሪል ኢብራሂም ወንድም እና የቀድሞ የጄም መሪ በሱዳን ጦር ነበር የተገደሉት።

እአአ 2003 ላይ የሱዳን መንግሥት ጥቁር አፍሪካውያንን ያገላል በማለት ጄም እና ኤስኤልኤም ነፍጥ አንስተው ከሱዳን ጦር ጋር ተዋግተዋል።

የሱዳን መንግሥት ደግሞ የአረብ ሚሊሻዎችን መልምሎ አሁን ፈጥኖ ደራሽ ሆኖ እየወጋው ያለውን ኃይል አሰማርቶባቸው ነበር።

ይህ በመንግሥት በሚደገፈው የአረብ ሚሊሻ እና በሁለቱ አማጺያን መካከል በዳርፉር የተደረገው ውጊያ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ዘር ማጥፋት ተብሎ ይገለጻል።

የመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጦር በቅርቡ የአገሪቱን ሁለተኛ ትልቋን ከተማ ኛላን ጨምሮ በዳርፉር የሚገኙ በርካታ ከተሞችን ተቆጣጥሯል።

ባለፈው ሳምንት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አረብ ያልሆነ በርካታ ሰዎችን በምዕራብ ዳርፉር መጨፍጨፋቸውን የሚያመላክት ሪፖርት ወጥቶ ነበር።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን በግድያው አለመሳተፉን እና ሰዎች የተገደሉት በጎሳ ግጭት ምክንያት ነው ብሏል።

ጄም እና ኤስኤልኤም አማጺ ቡድኖች የሱዳን ጦርን መቀላቀላውቸን ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸው “በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ገለልተኛ አቋማችንን በመቀየር በየትኛውም ግንባር የአገሪቱን ጦር ሠራዊት ወታደራዊ ዘመቻዎች ለመቀላቀል ቁርጠኛ ነን” ብለዋል።

ጄም እና ኤስኤልኤም እንደከዚህ ቀደሙ ጠንካራ የሆነ ወታደራዊ አቅም ባይኖራቸውም የእርስ በርሱ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው በግጭቱ ትልቅ ክስተት ነው።

በተጨማሪም ጅብሪል ኢብራሂም ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል ድጋፍ ታደርጋለች ከምትባለው የቻድ መሪ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

ጅብሪል ከቻድ መሪ ጀነራል መሐመት ዴባይ ጋር ያላቸውን ቅርበት ተጠቅመው ቻድ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ሊያደርጉ ይችላሉ።

የጄም መሪ ጂብሪል ኢብራሂም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሱዳንን ቢቆጣጠር አገሪቷ ትበታተናለች የሚል ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መቀመጫውን ምዕራብ ሱዳን በማድረግ መንግሥት መመሠረቱን ይፋ ሊያደርግ ይችላል የሚል ግምት አለ።