
18 ህዳር 2023, 08:22 EAT
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በርካቶችን እያጠቃ የሚገኘው የጉንፋን በሽታ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ፣ ኮቪድ ወይም የመተንፈሻ ሥርዓትን የሚያጠቃ በሽታ የመሆን ዕድሉ ሰፊ መሆኑ ተገለጸ።
ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ጉንፋን መሰል ሕመም አጥቅቷቸው ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በ6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡት ሰዎች ሳል፣ ትኩሳት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ቁርጥማት፣ የመገጣጠሚያ ሕመም እና ራስ ምታት፤ ሕጻናት ላይ ደግሞ የሆድ ሕመም እና የአፍንጫ ፈሳሽ የመሳሰሉ ተመሳሳይነት ያላቸው ምልክቶች እንደሚታይባቸው ገልጸው የበሽታውን ምንነት ለማረጋገጥ የ178 ሰዎች ናሙና ተወስዶ ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል።
በውጤቱ መሠረት 5 ሰዎች ላይ የኮቪድ በሽታ ሲገኝ፤ ምርመራ ከተደረገበት ናሙና 13 በመቶ በሚሆኑት ላይ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ተገኝቷል ብለዋል ኃላፊው።
አራት በመቶ በሚሆኑት ላይ ደግሞ የመተንፈሻ ሥርዓትን የሚያጠቃ ቫይረስ መገኘቱን ዶ/ር ሙሉጌታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ወደ ጤና ተቋማት ከመጡ ሰዎች ናሙናዎች ተወስደዋል። በአጠቃላይ ሕመም ታይቶባቸው ከመጡት መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ላይ የኮቪድ፣ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ወይም የመተንፈሻ ሥርዓት ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል” የሚሉት ዶ/ር ሙሉጌታ በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ከፍተኛ ቢመስልም አሃዙ ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የተለየ አይደለም ብለዋል።
- በሙስናና በሕግ ጥሰት የሚወነጀሉት የኬንያ ፖሊሶች ደሞዝ ሊጨመርላቸው ነው17 ህዳር 2023
- የእስራኤል ጦር የሁለት ታጋቾችን አስክሬን በጋዛ ማግኘቱን አስታወቀ12 ህዳር 2023
- እውቁ የሂፕ ሃፕ አቀንቃኝ ስኑፕ ዶግ ማጨስ ለማቆም ወስኛለሁ አለ17 ህዳር 2023
በርካቶችን የሚያጠቀው ጉንፋን መሰል በሽታ በሚያዝያ እና ግንቦት ወራትም ላይ እንደሚከሰት ገልጸው፣ በሽታው ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከባድ አለመሆኑን ተናግረዋል። “አልጋ እንዲይዙ የሚያደርግ ወይም ለሞት እና ለከባድ ጉዳት የሚዳርግ አይደለም።”
ቀላል የጉንፋን በሽታው ነው በማለት ወደ ጤና ተቋማት ለሕክምና የማይመጡ ሰዎች እንዳሉ ሆኖ፤ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ያሉባቸው ሰዎች ቁጥር ከጥቅምት በፊት ከነበሩት ወራት የስድስት በመቶ ጨማሪ ማሳየቱን ዶ/ር ሙሉጌታ ይገልጻሉ።
ጉንፋን መሰል በሽታዎች ወቅት እየጠበቁ በርካቶችን የሚያጠቁት ለመባዛት እና ለመተላለፍ ምቹ የሆኑ ወቅቶች ስላሏቸው መሆኑን ዶ/ር ሙሉጌታ ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ መምጣት ለምሳሌ የትምህርት ቤቶች መከፈት በሽታው እንዲሰራጭ ዕድል ይፈጥራል ይላሉ።
ሰዎች ከጉንፋን መሰሉ በሽታ እራሳቸውን ለመጠቅ በዋነኛነት የግል ንጽሕና በተለይ የእጅ ንህናን መጠበቅ እንዳለባቸው ዶ/ር ሙሉጌታ መክረዋል።
ሰዎች በሚበዙበት ቦታ ላይ ስንሆን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እራስን እና ሌሎችን በትንፋሽ ከሚተላለፉ በሽታውች ለመጠቅ አይነተኛ አማራጭ ነው ይላሉ የጤና ባለሙያው።
በዕድሜ የገፉ እና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ በማድረግ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም እንዲሁም ሕመም ሲያጋጥም በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።