በምርጫው የተሸነፉት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ እና አሸናፊው ጆሴፍ ቦአካይ
የምስሉ መግለጫ,በምርጫው የተሸነፉት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ እና አሸናፊው ጆሴፍ ቦአካይ

18 ህዳር 2023, 09:30 EAT

የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት የቀድሞው ከኮከብ የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ለሁለተኛ ዙር በተካሄደው የምርጫ ሂደት በጠባብ ልዩነት ተሸነፉ።

ፕሬዝዳንት ዊሃ የድምጽ ቆጠራው ውጤት መገለጹን ተከትሎ ወደ ተፎካካሪያቸው ጆሴፍ ቦአካይ ደውለው በምርጫው በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አሎት ብለዋቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት ንግግርም “ላይቤሪያውያን ማንን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፣ እኛም ድምጻቸውን ሰምተናል” በማለት የምርጫውን ውጤት እንደሚቀበሉት አሳውቀዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲው ዕጩ ጆሴፍ ቦአካይ ከተቆጠሩት ድምጾች መካከል በ28,000 ድምጽ በሥልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ዊሃን በመምራት ነው አሸናፊ መሆናቸው የታወቀው።

የቀድሞው ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ በሕዝብ ተመርጠው ባለፉት አምስት ዓመታት ላይቤሪያን በፕሬዝዳንትንት ሲመሩ ቆይተዋል።

ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የተፎካከሩት ፕሬዝዳንት ዊሃ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ጆሴፍ ቦአካይ በመሸነፋቸው በመጪው ጥር ሥልጣን ያስረክባሉ።

ዊሃ ከአምስት ዓመት በፊት ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡት ወጣት መራጮችን መሳብ በመቻላቸው የአሁኑን ተቀናቃኛቸውን በሰፊ የድምጽ ልዩነት በማሸነፍ ነበር።

ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ለውጥ ያመጡባቸዋል በተባሉት ሙስናን መዋጋት እና የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ካለመቻላቸው በተጨማሪ በአገሪቱ የቀጠለው የምጣኔ ሃብት ችግር ድጋፋቸውን ሸርሽሮ ለሽንፈት ዳርጓቸዋል።

ፕሬዝዳንት ዊሃ ሽንፈታቸውን በጸጋ መቀበላቸውን ባሳወቁበት የአምስት ደቂቃ ንግግር “አገራችንን የሚጠቅማትን ይህንን ዴሞክራሲያዊ ሂደት አከብራለሁ” በማለት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ካሏቸው አሸናፊው ጆሴፍ ቦአካይ ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ቀደም ብሎ እንዳሳወቀው ከተሰጠው ድምጽ ውስጥ ተቃዋሚው የ78 ዓመቱ የላይቤሪያ ጉምቱ ፖለቲከኛ ጆሴፍ ቦአካይ 50.89 በመቶ ድጋፍ ሲያገኙ፣ ፕሬዝዳንት ዊሃ ደግሞ 49.11 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።

የምርጫውን ውጤት ጠባብ ልዩነት በተመለከተ ፕሬዝዳንት ዊሃ በንግግራቸው “ይህ በአገራችን ውስጥ ጥልቅ መከፋፈል እንዳለ ያሳየል፤ ለእናት ላይቤሪያ አንድነት በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የሚያግባቡንን ጉዳዮች ላይ አብሮ መሥራት አስፈላጊ ነው” በማለት ለላይቤሪያውያን ጥሪ አቅርበዋል።

ማክሰኞ ዕለት የተካሄደውን ሁለተኛ ዙር የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን ተከትሎ አርብ ምሽት የላይቤሪያ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው ውጤት በመላው አገሪቱ ከሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች 99.58 በመቶው ነው።

የድጋሚ ምርጫው የተካሄደው ባለፈው ጥቅምት ወር በተሰጠው የመጀመሪያ ዙር ድምጽ ቆጠራ መሠረት ከሁለቱ ተፎካካሪዎች መካከል አንዳቸውም ከመራጩ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት ባለመቻላቸው ነው።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ በ7,000 ድምጽ ተፎካካሪያቸውን መብለጥ ችለው የነበረ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆን ድምጽ ግን አላገኙም ነበር።

ላይቤሪያ ከ20 ዓመታት በፊት እጅግ ከባድ እና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መቆየቷ ይታወቃል።

አሁን በላይቤሪያ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ማብቃት በኋላ የተደረገ አራተኛው ሲሆን፣ ከባድ ፉክክር እና በጠባብ ውጤት የተጠናቀቀ ምርጫ ነውም ተብሏል።