የፊንላንድ ድንበር ጠባቂዎች

18 ህዳር 2023, 11:07 EAT

ፊንላንድ የሩሲያ መንግሥት ሆነ ብሎ ስደተኞችን ወደ ድንበሬ እየላከ ነው በማለት ከሞስኮ ጋር የሚያዋስናትን አራት የድንበር በሮች ዝግ አደረገች።

ሄልሲንኪ እንደምትለው ከሆነ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) በመቀላቀሏ ሩሲያ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ወደ ፊንላንድ ስደተኞችን ሆነ ብላ ወደ ድንበር እየላከችባት ነው።

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ ፊንላንድ የድንበሯን በር መዝጋቷ “ትልቅ ስህተት ነው” ያሉ ሲሆን ሄልሲንኪ የሁለቱን አገራት “የሁለትዮሽ ግንኙነት እያበላሸች ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።

እንደ ፊንላንድ መንግሥት ከሆነ በዚህ ሳምንት ብቻ የሶሪያ፣ የየመን እና የኢራቅ ዜግነት ያሉባቸው 300 ስደተኞች በሩሲያ በኩል አድርገው ወደ ፊንላንድ ገብተዋል።

የፊንላንድ የድንበር ጥበቃ ዘብ ከአርብ ጀምሮ ቫሊማ፣ ኑኢጃማ፣ አማትራ እና ኒራላ በተባሉት የድንበር በሮች ላይ አጥር ማቆም ጀምሯል።

ፔስኮቭ ድንበር መዘጋቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ “የፊንላንድ ባለሥልጣናት የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያበላሽ መንገድን መርጠዋል። ሩሲያ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ፊንላንድን ተተናኩላ አታውቅም፤ ከፊንላንድ ጋር የሚያጋጨን ምንም አይነት ምክንያት የለም። በእኛ አረዳድ ይህ ትልቅ ስህተት ነው” ስለማለታቸው የሩሲያ ዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔቴሪ ኦርፖ የሩሲያ መንግሥት ሆን ብሎ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞችን ወደ ድንበር እያስጠጋ ነው ሲሉ ሞስኮን ከሰዋል።

ፊንላንድን ከሩሲያ የሚያገናኙ ሌሎች በሰሜናዊ የአገሪቱ ከፍል የሚገኙ ሁለት የድንበር በሮች ግን ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ከሩሲያ ወደ ፊንላንድ እየተሻገሩ ነው የሚባሉት ስደተኞች ሞስኮ በሕጋዊ መንገድ ከገቡ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ወደ ሆነችው ፊንላንድ ድንበር ተጉዘው ጥገኝነት ይጠይቃሉ ተብሏል።

የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔቴሪ ኦርፖ የሞስኮ ባለሥልጣናት የስደተኞቹን ጉዞ ሆነ ብለው እያመቻቹ ነው ይላሉ።

“እነዚህ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፤ በድንበር ጠባቂዎች ታጅበው ወደ ድንበር እንዲመጡ እየተደረገ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ፊንላድ ከሩሲያ ጋር 1340 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን በአውሮፓ ትልቁን ድንበር ትጋራለች።

እአአ 2021 ላይ ደግሞ የሩሲያ አጋር የሆነችው ቤላሩስን በተመሳሳይ ሁኔታ ወንጀላ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ደርሶባት ነበር።

በወቅቱ ፖላንድ እና ሊቱዌኒያ በቤላሩስ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እየመጡብን ነው ብለው ነበር።