አይዛክ አሕመድ እና ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ,አይዛክ አሕመድ እና ዐቢይ አሕመድ

18 ህዳር 2023, 08:14 EAT

በጎረቤት አገር ሱማሊያ የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆነው ግለሰብ ገጽታዬ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ዐቢይ አሕመድ ጋር በመመሳሰሉ የደኅንነት ስጋት ገብቶኛል ሲል ለቢቢሲ ሶማሊኛ ተናገረ።

“በመልክ ብቻ ሳይሆን በአባት ስም እንመሳሰላለን” የሚለው አይዛክ አሕመድ ሐሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ “ሕይወቴ ተቀይሯል” ይላል።

በምሥራቅ ሶማሊያ ዋይዬ የተባለች ወረዳ አስተዳዳሪ የሆነውን አይዛክ አሕመድ ትኩር ብሎ ያየው ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ሊመሳሰልበት ይችላል።

የአይዛክ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መልክ መምሰል ከሰሞኑ በሶማሊያ ፑንትላንድ ዋነኛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።

አይዛክ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመምሰሉ አንዳንዴ ፈገግ የሚያሰኙት አንዳንዴም የሚያበሳጩት አጋጣሚዎች እንደሚገጥሙት ይናገራል።

“አንዳንዴ ትልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሥራ ጉብኝት ከሞቃዲሾ መጥተው ሲያዩኝ ‘ዐቢይ አሕምድ’ ብለው ይቀልዱብኛል” በማለት ይናገራል።

በአንድ ወቅትም አንድ ባለሥልጣን ፎቶ አንስተውት ለቀድሞው የፑንትላንድ ፕሬዝዳንት ሲልኩላቸው፤ ‘ዐቢይ ፑንትላንድ ነው እንዴ?’ ብለው መልስ ሰጥተው እንደነበረ ያስታውሳል።

የአገሬው ሰው “አነጋግረውኝ ሶማሌ መሆኔ ሲረዱ ብቻ ነው የመልክ መመሳሰል እንጂ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አለመሆኔን የሚያረጋግጡት” ይላል አይዛክ።

አይዛክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ላለፉት አምስት ዓመታት በስሜ የሚጠራኝ የለም ይላል።

“ሰዎች ‘ዐቢይ’ እያሉ ይጠሩኛል። እኔ በሌላ ሰው ስም መጠራት አልፈልግም። ይሄ የዕለተ ተዕለት ሕይወቴን ቀይሮታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እየመሰልኩ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ባሉት ቦታ መገኘት ለደኅንነቴ ያሰጋኛል” በማለት ለቢቢሲ የሱማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ተናግሯል።

አይዛክ በሚኖርበት አካባቢ ሰዎች በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስም እንዲጠሩት እንደማይፈልግ ጨምሮ ይናገራል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወላጅ አባት አቶ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ,የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወላጅ አባት አቶ አሕመድ

“ከእኛ በላይ አባቶቻችን ይመሳሰላሉ”

የወረዳ አስተዳዳሪው አይዛክ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልክ መመሳሰል ሌላም ታሪክ አለው። አይዛክ አሕመድ እንደሚለው “ሰዎች የሚያስተውሉት መልካችን እና የአባታችን ስም መመሳሰልን ነው። የእኔ አባት እና የዐቢይ አባት መልካቸው ቁርጥ አንድ አይነት ነው” ይላል።

“አንድ ቀን አብሮኝ የሚሠራ እና ዘመዴ የሆነ ሰው ‘ይህን ሰው ታውቀዋለህ’ ብሎ አንድ ፎቶ ላከልኝ። ግራ ተጋባሁ፤ ለመለየት ተቸገርኩ። የላከልኝ ፎቶ የዐቢይ አባት ናቸው። መልካቸው ከአባቴ መልክ ጋር አንድ አይነት ነው። ልዩነታቸው የዐቢይ አባት ፊታቸው ላይ ጥቁር ነጥብ መኖሯ ብቻ ነው” በማለት አይዛክ ይናገራል።

አይዛክ አሕመድ እና ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ,አይዛክ አሕመድ እና ዐቢይ አሕመድ

“ኢትዮጵያ ብሄድ ፀጉሬን ተላጭቼ ነው”

አይዛክ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተመሳሳይ መልክ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እግሩን ቢያነሳ ውጤቱ ላያምር እንደሚችል ይገምታል።

በሶማሊያ ሰዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንደምመሳሰል ይህን ያክል ከተስማሙ “ኢትዮጵያ ብሄድም የሚጠብቀኝ የሄው ነው” የሚሆነው የሚለው አይዛክ፤ መልኩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲለይ “ኢትዮጵያ የምሄድ ከሆነ ፀጉሬን ተላጭቼ ነው” ይላል።

“ኢትዮጵያ የምሄድ ከሆነ ፀጉሬን እና ጺሜን ተላጭቼ እሄዳለሁ እንጂ ግራ መግባት በመፍጠር እራሴን ለአደጋ አላጋልጥም” ብሏል።