
19 ህዳር 2023, 09:00 EAT
ታማሚዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቅዳሜ ዕለት ጋዛ ከተማ ከሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል ለቀው እየሸሹ ይገኛሉ።
አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ቢገልጹም እስራኤል ግን አስተባብላለች።
የተኩስ ድምጽ እየተሰማ ብዙዎች በፈራረሱት መንገዶች ሲጓዙ ታይተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሐማስ የጤና ባለሥልጣናት በሰሜን ጋዛ በሚገኘው ጃባሊያ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች 80 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
እስራኤል ወደ መጠለያ ጣብያነት የተቀየረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትምህርት ቤት መምታቷን ባታረጋግጥም ምርመራ እያደረገች መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች ።
ቢቢሲ በጃባሊያ የሚገኘውን አል-ፋሁራ ትምህርት ቤት መሆኑን ባረጋገጠበት ምስል ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ይታያሉ።
በምስሉ ላይ ከ20 የሚበልጡ ተጎጂዎች የሚታዩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በአንድ የተወሰነ ክፍል ውስጥ ወለል ላይ ይታያሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን ባስጠለለው እና በኤጀንሲያቸው ስር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአንዱ “በርካታ የተገደሉ እና የተጎዱ ሰዎችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ምስሎችን” ማየታቸውን ተናግረዋል።
“እነዚህ ጥቃቶች የተለመዱ ሊሆኑ አይገባም፤ መቆም አለባቸው” ብለዋል።
በሌላ መረጃ ደግሞ በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት በጃባሊያ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ከ30 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በሪፖርቱ ላይ አስተያየት ባይሰጥም ሐማስን ዒላማ ለማድረግ በሚል ጃባሊያን ጨምሮ በጋዛ ያለውን ዘመቻ እያስፋፋ መሆኑን አስታውቋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጋዛ የሟቾች ቁጥር 12 ሺህ 300 መድረሱን ገልጿል። ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።
- በማደጎ ስዊድን ተወስዶ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አልበሙን የሠራው የግራሚ ዕጩ ዳንኤል ለማ19 ህዳር 2023
- በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዳሳሰቡት የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ18 ህዳር 2023
- በኢትዮጵያ አወዛጋቢ የነበረው ሬማ ለንደን ላይ ባቀረበው የሙዚቃ ዝግጅት መነጋገሪያ ሆነ18 ህዳር 2023
በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራ የተባበሩት መንግስታት ጥምር ቡድን በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኘውን አል-ሺፋ ሆስፒታልን ከጎበኘ በኋላ ተቋሙ “የሞት ቀጠና” ሆኗል ሲል ገልጿል።
ቡድኑ ለአንድ ሰዓት ያህል ሆስፒታሉን የገመገመ ሲሆን ጥቃት እንደደረሰበት ማየቱን እና በሆስፒታሉ መግቢያ ላይ የጅምላ መቃብር መመልከቱን ተናግሯል።
ከ80 ሰዎችም በላይ እንደተቀበሩበትም ተነግሯቸዋል።
በእስራኤል ጦር የተሰጠውን የውጡ ትዕዛዝ ተከትሎ በርካቶች ቢወጡም 300 በጠና የታመሙ ህሙማን በአል-ሺፋ ሆስፒታል ውስጥ ቀርተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቡድን በቀሪዎቹ ታማሚዎች እና ሰራተኞች ወደ ሌሎች ተቋማት በአስቸኳይ ለማዘዋወር እየሞከረ መሆኑን አስታውቋል።
በሆስፒታሉ የሚገኝ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደገለጸው “መንቀሳቀስ የማይችሉ ታካሚዎች እና በጣም ጥቂት ዶክተሮች” ብቻ ቀርተዋል።
“እጃችንን ከፍ አድርገን ነጭ ባንዲራ ይዘን ነበር” ሲል በአልሺፋ የነበረው ጋዜጠኛ ከድር ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ምሽቱ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የፍንዳታው እና የተኩሱ ድምጽ በጣም አስፈሪ ነበር። ቡልዶዘሮቹ በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ትላልቅ ጉድጓዶች ቆፍረዋል።”
ቀደም ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 120 ታማሚዎች በሆስፒታሉ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።