የሩስያ ህንጻ

19 ህዳር 2023, 08:53 EAT

ቅዳሜ እለት ወደ ሞስኮ እያቀና የነበረ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮላን (ድሮን) በመከላከያ ሰራዊታቸው ተመትቶ መውደቁን የሩስያ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ድሮኑ በዋና ከተማዋ ሰሜናዊ ምስራቅ ዳርቻ ላይ በሚገኘው ቦጎሮድስኪ ግዛት ውስጥ እንዲቀለበስ መደረጉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌይ ሶብያኒን ሞትም ሆነ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳደረሰ ገልጸዋል።

ሩስያ ካስወነጨፈቻቸው 38 ኢራን ሰራሽ የሻሄድ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ውስጥ 29ኙ መመታታቸውን ዩክሬን ካስታወቀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው ሩሲያ ይህንን ያለችው።

ቅዳሜ ዕለት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የአየር ኃይላቸው የሩሲያን ድሮኖች መትተው በመጣላቸው አሞካሽተዋቸዋል። በስድስት ሳምንታት ውስጥ ሩሲያ ካስወነጨፈቻቸውም ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነም ተነግሯል።

ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ “ ትክክለኛ በሆነ ሁኔታ አነጣጥራችሁ መምታታችሁ ለዩክሬን ህይወት ነው” ብለዋል።

ነገር ግን የክረምቱ ወቅት እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ጥቃቷን የበለጠ እንደምታጠናክርም አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ እንዳሉት ሩሲያ በዩክሬን የኃይል መሰረተ ልማት ላይ በክረምት ወቅት ለምታደርሰው ጥቃት ሚሳኤሎችን እያከማቸች ነው።

አርብ ምሽት የተፈጸመው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በዩክሬን ከ400 በሚበልጡ ከተሞች እና መንደሮች ላይ የኃይል መቆራረጥን አስከትሏል። ጥቃቱ በተጨማሪም በደቡብ ኦዴሳ የሚገኘው የነዳጅ ማከማቻ ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ይህም ከ1 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎችን መብራት አልባ አድርጓቸዋል።

ዩክሬን በዶኔትስክ ክልል ውስጥ ወደ 21 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሌላቸው የገለጸች ሲሆን በተጨማሪም በዛፖሪዝሂያ ክልል 63 ሰፈራዎች ተቋርጦባቸዋል።

ሩስያ ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ ባደረሰቻቸው ጥቃቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናውያንን ለሰዓታት መብራት አልባ ያደረጋቸው ሲሆን ይህም አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜንም ለመጋፈጥ ተገደዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ጦሯ በዲኒፕሮ ወንዝ ምስራቅ ዳርቻ ላይ ያሉ ስፍራዎችን እየተቆጣጠረ ነው ብላለች።