ዳንኤል ለማ

19 ህዳር 2023, 08:05 EAT

ዳንኤል ለማ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ ነው። ‘አዲስ’ የተሰኘ አልበሙ በቅርቡ ተለቋል። በማደጎ በስዊድናዊ ቤተሰቦች ያደገው እና በምዕራቡ ዓለም በስፋት የሚታወቀው ድምጻዊው በትውልድ አገሩ አልበም ሲሠራ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የግራሚ ሽልማት ዕጩው ዳንኤል ስለ አዲሱ አልበሙ፣ ስለ ሙዚቃ ሕይወቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ቢቢሲ፡ በኢትዮጵያ አልበም መቅረጽ ምን ስሜት ፈጠረብህ?

ዳንኤል፡ ማድረግ ከምፈልጋቸው ነገሮች ዝርዝር ውስጥ አንደኛውን ቦታ የምሰጠው ነገር ነበር። በምፈልገው መንገድ መሥራት እንድችል የሚረዱኝ በሙዚቃውም፣ በግልም ጓደኞች ለማፍራት ጊዜ ወስዷል። በጣም ነው ደስ ያለኝ።

ቢቢሲ፡ ለምን አሁን አልበሙን ኢትዮጵያ ለመቅረጽ ወሰንክ?

ዳንኤል፡ የረዥም ጊዜ ሕልሜ ነበር። ዕድሉን እስካገኝ ነበር ስጠብቅ የነበረው። ያ ማለት ሙዚቀኞች ማወቅ ነበረብኝ፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ እና ባህል መረዳት ነበረብኝ። በተወሰነ ደረጃ አውቀዋለሁ፤ ግን ሁሌም ተማሪ ነኝ። ትክክለኛው ሰዓት መምጣት ነበረበት። አንድ ነገር ከማድረጌ በፊት የምሠራውን ማወቅ እፈልጋለሁ። ስለዚህ አሁን ሥራዬን ኢትዮጵያ ውስጥ መቅረጽ ለእኔ ያለውን ዋጋ ያህል ሳይኖረው በፊት መቅረጽ አልፈለኩም።

ቢቢሲ፡ ምን ያህል ጊዜ ነው የወሰደብህ?

ዳንኤል፡ መጀመሪያ የቀረጽነው በ2018 (እአአ) ነው። አንድ ዘፈን ቀረጽን። ከዚያ ወረርሽኙ፣ አለመረጋጋቱ መጣ። ወደ 2020 አካባቢ በድጋሚ ተጀመረ። አዲስ አበባ እና ስዊድን ስመላለስ ነበር። አንዴ አዲስ አበባ ስቱዲዮ ስገባ ግን ብዙም ጊዜ አልወሰደም።

ቢቢሲ፡ አልበሙን በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ላንተ የማይረሳው ወይም ከፍታ የምትለው የትኛው ቅጽበት ነው?

ዳንኤል፡ ብዙ ነገሮች ነበሩ። በጣም የማልረሳው ግን ናርዶስ ስትዘፍን የቀረጽናትን ቅጽበት ነው። በተለያዩ አገራት ስቱዲዮዎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ነው የቀረጽኩት። ስቱዲዮ ውስጥ መቅረጽን ብወደውም አዲስ ነገር አይደለም። ያ ቅጽበት ግን የተለየ ነው። ስሜት ይነካል። እየዘፈነች ሳለ ያሰብኩት ሁሉንም ነገር ነው። ‘አዲስ አበባ እየቀረጽኩ ነው። መምጣት የምፈልግበት ቦታ መጣሁ’ ብዬ አሰብኩ። ስትዘፍን፣ በጣም በጥልቀት ተነካሁ። ስሜታዊ ሆንኩ። እኔ ደግሞ በቀላሉ ስሜታዊ የምሆን ሰው አይደለሁም። የብዙ ነገሮች ድምር ነው። በጣም ኃይለኛ ስሜት ነበር የተሰማኝ።

ቢቢሲ፡ ከምትፈልጋቸው ነገሮች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃህን መቅረጽ አንዱ እንደሆነ ነግረኸኛል፤ ሂደቱ የጠበቅከውን ያህል ነበር?

ዳንኤል፡ አዎ። ረዥም ጊዜ በመጠበቄ ደስ ያለኝም ለዚያ ነው። በብዙ መንገድ ከጠበቅኩት በላይ ነው የሆነው። ይሆናሉ ብዬ ያልጠበቅኳቸው ብዙ ነገሮች ሆነዋል። እስከተወሰነ ደረጃ ትዘጋጃለሽ አይደል? ግን ከተዘጋጀሽውም በላይ ያልፋል። እንደዚያ ሲሆን ቅጽበቱን ማጣጣም ነው።

ቢቢሲ፡ ወደ ትውልድ አገርህ ለመመለስህ ምልክት የሆነ ወይም ‘homecoming’ አልበም ልንለው እንችላለን. . .

ዳንኤል፡ [ሳቅ] እንደዛ ነገር ነው። ከማንም በላይ ይሄ አልበም ለእኔ ነው።

ቢቢሲ፡ ከኢትዮጵያ አድማጮችህ በበለጠ ከሚያውቅህ የውጭው አገር አድማጭ እና ከኢትዮጵያዊም አድማጭ ምን ትጠብቃለህ?

ዳንኤል፡ እውነቱን ልንናገር፣ ይሄ አልበም የተሠራው ከማንም በላይ ለእኔ ነው። ሰዎች ከወደዱት በጣም ደስ ይለኛል። ካልወደዱትም በጣም ደስተኛ ነኝ። ስለ አልበሙ እንዲሰማኝ የምፈልገው አሁን እንደሚሰማኝ ነው። ማሳካት የምፈልገውን አሳክቻለሁ። ለእኔ ጉዞ፣ ለእኔ ነፍስ የሚያስፈልገኝ ይሄ ነበር። ሰዎች እንዲሰሙት፣ እንዲወዱት እኮ እፈልጋለሁ። ግን ደግሞ በዚህ ዘመን የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ አውቃለሁ። ይሄ ብዙ ጊዜ የሚባል ነገር ይሆናል።

ዳንኤል ለማ

ቢቢሲ፡ የአልበሙ መጠሪያ ‘አዲስ’ ነው። ‘ወደ አዲስ አበባ’፣ ‘ጎንደር’፣ ‘ትዝታ’ የሚሉትን ዘፈኖች ስሰማ ለእናት አገርህ ውዳሴ እያቀረብክ ነው የሚመስለው። በዚህ አልበም ምን ማለት ነው የፈለግከው?

ዳንኤል፡ [ሳቅ] አልበም ውስጥ የሙዚቃ ስብስብ መሥራት ደስ ይለኛል። ለፈጠራ፣ የሚያነሳሳኝ ያ ነው። የሙዚቃ ስብስብ ሲሠራ አንዳች መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል። እኔ ብቻ እሆናለሁ እንዲህ የሚሰማኝ መሰለኝ። ግን በዚያ መንገድ ሙዚቃው ሲጻፍ ነው ጥሩ። የመጀመሪያዎቹ አራት ሙዚቃዎች ወደ አዲስ አበባ ስለተደረገ ጉዞ ያወሳሉ። ከዚያ በኋላ አልበሙን አስፍተን ስናየው ወደ ኢትዮጵያ ስለሄደ ሰው ነው። በእርግጥ ወደ የትኛውም አገር ስለመሄድ ሊሆን ይችላል። በሆነ መንገድ እንግዳ መስሎ ወደሚታየው አገር ስለሚሄድ ሰው ነው። በተቀሩት ሦስቱ ዘፈኖች የምንሰማው አንዲት ሴት ተዋውቆ ወደ አገሩ ሲመለስ ሊያስታውሳት ሲሞክር ነው። እንደ ፍቅር ታሪክ ልንወስደው እንችላለን። ግን ደግሞ አገርን፣ ስሜትን፣ ተሞክሮን ለማስታወስ ስለመሞከርም ነው። አብዛኞቹ ዘፈኖች ወደ ኢትዮጵያ ስለመሄድ ናቸው። እናም ስለ ደስታ፣ ስለ ማጣት፣ ነገሮች ካሉበት ሁኔታ ጋር ሕይወትን ስለማስታረቅም ነው።

ቢቢሲ፡ አብዛኞቹ ሙዚቃዎች የአዝማሪ ሙዚቃ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ከብሉዝ እና ከሌሎችም ስልቶች ጋር ያዋሃዱ ናቸው። ከዚህ ቀደም የምትሠራውን የብሉዝ፣ ጎስፕል ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር ለማስተሳሰር እየሞከርክ ነው?

ዳንኤል፡ እየሞከርክ ነው ወይ? በማለትሽ አመሰግናለሁ። ምክንያቱም እየሞከርኩ ነው። እርዳታም ተሰጥቶኛል። የማላውቀው ነገር ውስጥ ስለማልገባ። ካልለመድሽው ባህላዊ ሙዚቃ ጋር ሙዚቃን ለማዋሃድ ስትሞክሪ ምናልባትም ልትሳሳች ትችያለሽ። ስለዚህ የትኞቹን የሙዚቃው ክፍሎች ነው መቀየጥ የምንችለው የሚለውን ተወያይተናል። ይህም ማድረግ የማልችለውን እንዳላደርግ እና ያልሆንኩትን ሰው ለመሆን እንዳልሞክር ነው። እናም አክብሮት በተሞላው መንገድ ከባህል ጋር ሙዚቃውን ለማዋሃድ እየሞከርኩ ነው። ግሩም መዝሙር በጣም ነው የረዳኝ። ምን ይደረግ፣ ምን አይደረግ የሚለውን ብዙ ተወያይተናል። ለጥያቄሽ መልሱ ግን፣ እየተለወጥኩ ነው አልልም። እንደ ቀድሞው ዓይነት ሙዚቃ ነው የምሠራው። ግን ደግሞ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ሰምቻቸው ከወደድኳቸው ሙዚቃዎች ጋር እያዋሃድኩት ነው።

ቢቢሲ፡ ወደ ስዊድን በማደጎ ከመወሰደህ በፊት የተወለድከው ኢትዮጵያ ነው። አሁን ደግሞ ትልቁ ሕልሜ የምትለውን ኢትዮጵያ መጥቶ አልበም መሥራትን አሳክተሀል። ይሄን አልበም በዋናነት ቢሰሙልኝ የምትላቸው ሰዎች አሉ? ምናልባትም ከቤተሰቦችህ መካከል ሊሆን ይችላል. . .

ዳንኤል፡ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። . . . [ዘለግ ላለ ደቂቃ አስቦ] . . . እናቴ በሕይወት ኖራ ብትሰማው መልካም ነበር። ደስ የሚል ነገር ነበር። ልክ እንደእኔ በማደጎ ተወስደው ያደጉ እና ከኢትዮጵያ ጋር ለመተሳሰር እየሞከሩ ያሉ ዳያስፖራዎች አሉ። የእነሱ ታሪክ ከእኔ የተለየ ነው። ግን ጊዜ ከወሰዱ እና ካደመጡ ምናልባት ዳግመኛ መተሳሰር እንደሚቻል ይሄ አልበም ማሳያ ይሆናል።

ቢቢሲ፡ ‘7th Son’ የሚለው ዘፈን በጣም በጥልቅ ስሜት የተሞላ ነው። ከአገር መለያየትን፣ እንግዳ መሆንን ይገልጻል። ቋንቋ አለማወቅን አንድ የዘፈኑ ግጥም ላይ ትጠቅሳለህ። ይህን ሙዚቃ የጻፍከው ከራስህ ሕይወት ተነስተህ ይሆን?

ዳንኤል፡ ወደ ኢትዮጵያ ለዓመታት ተመላልሻለሁ። ለመጀመሪያ የሄድኩት በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሆኜ ነው። ሌላ ዓለም ላይ እንዳለሁ ነበር የተሰማኝ። በአንድ በኩል ሲታይ ሰዎቹ የሚመስሉት እኔን ስለሆነ ወደ አገሬ እንደተመለስኩ ተሰማኝ። ሆኖም ግን አገሪቱ እኔ ከማውቀው ዓለም የተለየች ነበረች። እዚህ ነው የተፈጠርኩት የሚል ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሰዎቹን ባልረዳቸውም ከሰዎቹ፣ ከመሬቱ፣ ከአገሩ ጋር እንደተሳሰርኩ ይሰማኝ ነበር። የሆነ ተቃርኖ አለው። አሁንም ያንን ስሜት ለመረዳት እየሞከርኩ ነው። ምናልባትም ዕድሜ ልኬን ለመረዳት የምሞክረው ነገር ይሆናል።

ቢቢሲ፡ ‘ትዝታ’ የሚለው ሙዚቃ ማስታወስ የምትፈልጋቸው ትውስታዎችን እየፈለግክ ይመስላል።

ዳንኤል፡ እሱ ዘፈን በብዙ ሂደት ነው ያለፈው። ‘Memories’ እና ‘Mountain Rose’ የተባሉት ሙዚቃዎችም ከትውስታ ጋር ስለመቆየት ያወሳሉ። ስሜቱን በተለያየ መንገድ ለመግለጽ ነው የጻፍኳቸው። አንድን ነገር በተለያየ መንገድ ደጋግሞ፣ ደጋግሞ መናገር በይው። የገጠመኝን ነገር ላለመርሳት የሚደረገው ሙከራ አካል ነው።

ቢቢሲ፡ የትኛው ሙዚቃ የበለጠ አንተን ይገልጻል?

ዳንኤል፡ ብዙ ጊዜ አልበም ስሠራ ሙዚቃዎቹን ደጋግሜ ደጋግሜ እሰማና ስጨርስ ስለሚታክተኝ ለዓመታት መልሼ ላልሰማቸው እችላለሁ። ለመምረጥ ቢያስቸግርም ‘7th Son’ በስተመጨረሻ የያዘው ቅርጽ ደስ ይለኛል። የናርዶስን ድምጽ በጣም ነው የምወደው። አልበሙ ውስጥ ድምጿ መኖሩ አስደስቶኛል። በሌሎቹ ሙዚቀኞችም ደስተኛ ነኝ። እጃቸውን ዘርግተው ነው የተቀበሉኝ። ክብር ይሰማኛል።

ዳንኤል ለማ

ቢቢሲ፡ ሕጻን እያለህ ነው በማደጎ ከኢትዮጵያ የተወሰድከው። ላንተ ከአገርህ እና ከማንነትህ መነሻ ርቆ ማደግ ምን ማለት ነበር?

ዳንኤል፡ ሕጻን ስለነበርኩ ስሄድ አላስታውስም። ለእኔ ኢትዮጵያ የሆነች ምናባዊ አገር ነበረች። አብዛኞቹ የማደጎ ቤተሰቦች ስለ ልጆቹ ትውልድ አገር የሚያወሩ አይመስለኝም። ‘የሕጻናት ማቆያ ደረጃ ላይ ነው የተገኘኸው’ ከሚል በዘለለ ታሪካቸው ብዙዎች አይነገራቸውም። የእኔ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ቤተሰቦቼ ግልጽ ነበሩ። ይሄ ኢትዮጵያ ያለው ቤተሰብህ ነው ብለው ፎቶ ያሳዩኝ ነበር። ደብዳቤ እጽፍላቸው፣ እነሱም ይመልሱልን ነበር። መቼ እንደሆነ ነው እንጂ ያላወቅኩት አንድ ቀን ኢትዮጵያ እንደምሄድ አውቅ ነበር። ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ የስዊድን መንግሥት እንዳንሄድ ነገረን። ወደ ግዳጅ ውትድርና እንዳንወሰድ ማድረግ እንደማይችሉ ነገሩን። በደርግ ዘመን ነበር። ስለዚህ ያኔ አልሄድኩም።

ቢቢሲ፡ ፍቅር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ እያደጉም ቢሆን አእምሮ ለምን በማደጎ ተሰጠሁ ብሎ መጠየቁ ይቀራል ብዬ አላስብም። በዚያ ላይ ፈጽሞ እንግዳ በሆነ የነጭ ዓለም ውስጥ ጥቁር ልጅ ነህ።

ዳንኤል፡ እንደ ልጅ፣ ከኢትዮጵያ ነኝ የሚለው ነገር አእምሮዬ ላይ ቀድሞ የሚመጣ አልነበረም። ኢትዮጵያ ምናባዊ ቦታ ናት ብዬ አምኛለሁ። አንድ ቀን ሄጄ የምጎበኛቸው ሰዎች ፎቶግራፍ እጄ ላይ አለ። ቤተሰቦቼ ናቸው። ግን ሥጋዬ እና ደሜ የምለው ስዊድናዊ ቤተሰቦቼን ነበር። ልጅ ሳለው ቤተሰቦቼ የምለው፣ ቤቴ የምለው እነሱን ነበር። በነጭ አገር ውስጥ ጥቁር ልጅ መሆን ግን በየቀኑ የምኖረው እውነታ ነበር። ያኔ ስዊድን ከባድ እና ከአሁኑ የተለየም አገር ነበር። ብዙ የውጭ አገር ዜጎች አልነበሩም። ጥቁሮችም በብዛት አልነበሩም። ብዙ ችግር ይገጥመኝ ነበር ግን ማለት አልችልም። ሰዎች ከእኔ በላይ ብዙ ችግሮች እንደነበሯቸው አውቃለሁ። እንዴት ልግለጸው ብቻ. . . አንቺ ለረዥም ጊዜ ነጮች በሚበዙበት አገር ኖረሻል?

ቢቢሲ፡ አይ አልኖርኩም።

ዳንኤል፡ እንዴት መሰለሽ፣ የሆነ ዓይነት ‘Minority Stress’ ትላበሻለሽ። አንዳንዴ የሆነ ስሜት ይሰማሽ እና ቃል ሳታገኚለት ትቆያለሽ። ከዚያ ልክ ቃሉን ስትሰሚ ‘አዎ እሱ ስሜት ነው የሚሰማኝ’ ትያለሽ። የሆነ ሁልጊዜም ጫፍ ላይ የመሆን ስሜት ልለው እችላለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ስሄድ ነው ይሄን ያስተዋልኩት። የሆነ ነገር ከላዬ ላይ እንደተነሳ ነው የተሰማኝ። የሆነ ነገር ተጭኖሽ፣ እንደ ተጫነሽ ግን ሳታውቂው ቆይተሽ ሲነሳልሽ ያለው እፎይታ ነው። ወደ አገር ቤት መሄድን ትናፍቂያለሽ። እነዚህን ስሜቶች ለማስታመም ሙዚቃን በማግኘቴ ዕድለኛ ነኝ።

ቢቢሲ፡ በአንድ ወቅት ከማደጎ ጋር በተያያዘ በሠራነው ተከታታይ ዘገባ፣ ቤተሰቦች ከተለያዩ በኋላ ለመገናኘት የሚከፍሉትን መስዋዕትነት፣ ከወላጅ ተለይቶ ማደግ እና መኖር የሚያሳድረውን የሥነ ልቦና ጫና እና ተያያዥ ጉዳዮችን ዳሰን ነበር። የሁሉም ሰው ታሪክ እና ተሞክሮ አንድ እንደማይሆን እረዳለሁ። ግን አንተ እየነገርከኝ ያለኸው ስሜት የተለየ ይመስላል።

ዳንኤል፡ ስሄድ ገና የሦስት ወር ሕጻን ነበርኩ። በዕድሜ ከፍ ብሎ ከአገር ከመውጣት ይለያል። ቅድም አልበምህን ማን እንዲሰማው ትፈልጋለህ? ስትይኝ ዘለግ ላለ ደቂቃ ያሰብኩትም ለዚህ ነው። ሁሉም ሰው ታሪኩ የተለያየ ነው። ብዙ የማደጎ ልጆች በስዊድን እና በሌሎችም ቦታዎች አግኝቻለሁ። ተሞክሯቸው የተለያየ ነው። የእኔ ታሪክ ለየት ያለ ነው። ውስብስብ አይደለም ማለት እችላለሁ።

‘የትውልድ እናትህ በወቅቱ በጣም ድሃ ስለነበረች አንተን መንከባከብ ስለማትችል፣ ይሄ ላንተ የተሻለ ዕድል ነው ብላ በሦስት ወርህ በማደጎ ወደ ስዊድን መጣህ’ የሚል ታሪክ ተነገረኝ። ‘አሁን ቤተሰቦችህ እኛ ነን። እንወድሀለን። እንንከባከብሀለን’ ተባልኩ። ‘ፎቷቸው ይኸውልህ፣ ደብደቤ ከጻፍክላቸው ይመልሱልሀል። አንድ ቀን ሄደህ ታያቸዋለህ’ ተባልኩ። አእምሮዬ እንግዳ ነገር ነው ብሎ አላሰበውም። ልክ ወላጅ እናቴን ሳገኛት ነው ጥያቄዎች የተፈጠሩብኝ።

እንዴ ይሄ ነገር ትንሽ እንግዳ ነው ብዬ አሰብኩ። ከዚያ በፊት የማስበው ወላጅ እናቴ ሌላ ቦታ እንዳለ ልጇ እንደምታየኝ ነው። ትስስራችንን አልቆረጠችውም። ትልቅ ዕድል እንዳገኝ ነው ያሰበችው። በማደጎ ያደገ የሥጋ ወንድም አለኝ። አብረን ብንሆን የተሻለ እንደሚሆን ያሰበች ይመስለኛል። እውነት ነው ውስጤ ስላለው ጥያቄ ብዙ አስቤያለሁ። ግን ኢትዮጵያ ነው መሆን የነበረብኝ እያልኩ አላስብም ነበር። አንዳንዴ ሰዎች በሕይታቸው ላሉ ችግሮች በማደጎ በማደጋቸው ላይ ማመኻኘት ይቀላቸዋል። እኔ መጀመሪያ ወላጅ እናቴን ሳገኛት፣ እኔ እና እሷ የተለያየን ሰዎች መሆናችንን ነው ያስተዋልኩት። እኔ እና እሷ ዓለምን የምናይበት መነጽር የተለያየ ስለሆነ ያሉኝ አብዛኞቹ ጥያቄዎች ትርጉም አልባ ሆኑብኝ።

ዳንኤል ለማ

ቢቢሲ፡ ላንተ ማንነት እንዴት ይገለጻል?

ዳንኤል፡ በሙያ ሙዚቀኛ ነኝ። የማንነት ጥያቄ ራስሽን የምታይበት መንገድ እና ከሰዎች እንዲሁም ከዓለም ጋር የምትገናኚበትም መንገድ ነው። በዚያ መንገድ ካየነው ማንነት ከሚለው ለመውጣት እሞክራለሁ። እኔ ይህ ነኝ ወይም ያ ነኝ ካልኩ ከሰዎች ጋር የምገናኝበትን መንገድ እገድባለሁ።

ቢቢሲ፡ ከሙዚቃ ጋር የተዋወቅክበት የሕይወትህ ክፍል የቱ ነው?

ዳንኤል፡ አባቴ ሙዚቀኛ ባይሆንም ሙዚቃ በጣም ይወዳል። ሁሌም ቤታችን ሙዚቃ ይከፈታል። ሁሌም ጃዝ፣ ጎስፕል፣ ብሉዝ ይሰማል። ልጅ እያለሁ ከበሮም መጫወት ጀመርኩ።

ቢቢሲ፡ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር እንዴት ተዋወቅክ?

ዳንኤል፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሰማሁት አንድ ሰው ‘Desert Blues’ የተባለ የአፍሪካ ሙዚቃ ስብስብ አልበም ሰጥቶኝ ነው። ኦሙ ሳንጋሪ፣ አሊ ፋርካ ቱሬ እና ሌሎችም ሙዚቀኞች ነበሩበት። እዚያ አልበም ላይ የመሐሙድ አሕመድ ‘ኧረ መላ መላ’ ነበረበት። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት የኢትዮጵያ ሙዚቃ እሱ ነው። ከሌሎቹ ሙዚቃዎች ጋር ሲነጻጸር የሆነ ምሥጢራዊ ድምጽ አለው። [ሳቅ] አሁንም ስሰማው እንደዚያ ይሰማኛል።

ቢቢሲ፡ ስንት ዓመትህ ነበር?

ዳንኤል፡ እእእ. . .17 ብሆን ነው።

ቢቢሲ፡ ሙዚቃውን ስትሰማ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ሄጄ አልበም እቀርጻለሁ ብለህ አስበሀል?

ዳንኤል፡ በፍጹም። በፍጹም። መጀመሪያ እንደዚያ አልተሰማኝም። ምሥጢራዊነቱ እንዳለ ሆኖ ሩቅ ያለ ነገርም ነበር። ስሰማ ያደግኩት ሙዚቃ የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃ፣ የደቡብ አፍሪካ ሙዚቃ ቢሆን ለመተሳሰር ቀላል ነው። ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲመጣ ግን ጊዜ ይወስዳል፣ መውደድ ከመጀመሬ በፊት መረዳት የነበረብኝ ብዙ ነገሮች ነበሩ። የተለየ ስለሆነ መጀመሪያ ልረዳው ይገባል ብዬ ነው ያሰብኩት።

ቢቢሲ፡ በተለየ መንገድ ተጽዕኖ ያሳደረብህ የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ አለ?

ዳንኤል፡ አሁንም የመሐሙድ አድናቂ ነኝ። ሙዚቃዎቹን እወዳቸዋለሁ። ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር የበለጠ ያስተዋወቀኝ ‘ኢትዮፒክስ’ ነው። የጂጂ አልበም ሲወጣ ትዝ ያለኛል። ግን ተጽዕኖ ያሳደረብኝ አለ አልልም።

ቢቢሲ፡ የትኞቹ ሙዚቀኞች ናቸው ባንተ ላይ ተዕጽኖ ያሳደሩት?

ዳንኤል፡ ጊታር እጫወታለሁ። የድሮ ብሉዝ እና ፎክ ሙዚቃ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። ሙዚቃ ስሰማ ሙዚቀኛው ማን ተጽዕኖ እንዳሳደረበት አጠናለሁ። ከዚያ ተጽዕኖ ያሳደረውን ሰው ሙዚቃ ደግሞ እሰማለሁ። ወደ ምንጩ እየተጓዝኩ ነው የምሄደው። ሚሲሲፒ ጆን ኸርት፣ ብላይንድ ዊሊ ሜክቴል፣ ቦብ ዲለን የመሳሰሉትን ነው የምሰማው። የአሜሪካ ፎክ ሙዚቃ ናቸው የምሰማቸው። በጎስፕል፣ ብሉዝ እና ጃዝ መካከል ሙዚቃ የሚሠራበት ዘመን።

ዳንኤል ለማ

ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም ሙዚቃህ አይታወቅም። ወይም ገና ብዙም አልተሰማም። አዲሱ አልበም ይሄን ይለውጣል ብለህ ታስባለህ?

ዳንኤል፡ አንዳንድ ሰዎች ሊወዱት ወይም ትርጉም ሊሰጣቸው ይችላል። ግን የእኔ ሐሳብ አልበሙን ለራሴ መሥራት ነው። አልበሙ ምን እንደምሠራ ሰዎች የሚያውቁበት ይሆናል። አብረን እናያለን። [ሳቅ]

ቢቢሲ፡ ለግራሚ ሽልማት ታጭተህ ነበር። መታጨትህ እንደ ሙዚቀኛ በሥራህ ላይ የለወጠው ነገር አለ?

ዳንኤል፡ ከ15 ዓመታት በፊት አሜሪካ ኖሬ ነበር። ለአራት ዓመት ገደማ። ከዚያ ወደ ስዊድን ተመለስኩ። ጓደኛዬ ፊልም እየሠራ አንድ ሁለት ማጀቢያ ሙዚቃ ሠርቼ በዚያው ብዙም ያላሰብኩበትን አልበም ሠራሁ። እሱ አልበም በአውሮፓ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ። ለግራሚ መታጨቴ ግን የምሠራውን ሙዚቃ አለወጠውም። ይሄን ሙያ እወደዋለሁ፣ የመረጥኩትም ነው። የወደድኩት እና የመረጥኩት ሙያ መጣመራቸው ደስተኛ ያደርገኛል።

ቢቢሲ፡ ትልቁ ስኬቴ የምትለው ምንድን ነው?

ዳንኤል፡ ትልቁ ስኬቴ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ የምሠራውን መውደዴ ነው። ያኮራኛል። ሁሌም አዲስ ነገር ይገጥመኛል።

ቢቢሲ፡ የመጨረሻ ጥያቄዬ፣ የአንተ የምንጊዜም ምርጥ ሦስት አልበሞች እና ዘፈኖች የትኞቹ ናቸው?

ዳንኤል፡ [ረዥም ሳቅ] መምረጥ ከባድ ነው። ለአሁኑ ግን፣ ሦሰት ምርጥ አልበሞቼ የቦብ ማርሌይ እና ዘ ዌለርስ ‘ናቲ ድሬድ’፣ የቦብ ዲለን ‘ታንግልድ አፕ ኢን ብሉ’ እና የጆኒ ሜቸል ‘ብሉ’ ናቸው። ሦስት ምርጥ ዘፈኖች ደግሞ የሳም ኩን ‘ኤ ቼንጅ ኢዝ ጎነ ካም’፣ የጆኒ ሚቼል ‘ቦዝ ሳይድስ ናው’ እና የጆርጅ ሃሪሰን ‘ሰምቲንግ’ ናቸው።