
20 ህዳር 2023, 08:26 EAT
ሐማስ መስከረም 26 ካደረሰው ጥቃት በኋላ የወሰዳቸው ታጋቾች ወደ ጋዛ ትልቁ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚያሳይ ነው ያለችውን ከስፍራው የተቀረጸ ቪዲዮ (ሲሲቲቪ) የመከላከያ ሰራዊቱ አሳይቷል።
ከታጋቾቹ አንዷ የሆነችውም ወታደር በሆስፒታሉ መገደሏን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
የ19 ዓመቷ ኖአ ማርሲያኖ የተገደለችው ቀላል ጉዳት ደርሶባት ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል የሐማስ ማዘዣ ጣብያ ነው ያለችው ዋሻ በሆስፒታሉ መገኘቱን ተናግራለች። ሐማስም ሆነ የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ይህንን ፍጹም ሐሰት ነው ሲሉ አይቀበሉትም።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እሑድ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያቀረበውን ቪዲዮ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
የሠራዊቱ ዋና ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ “በእኛ መረጃ መሠረት አልሺፋ አካባቢ ወደሚገኝ ቤት ተወስዳ እንደነበር ለኖኦ ቤተሰብ ዛሬ አሳውቀናል” ብለዋል።
“በአካባቢው የእስራኤል ጦር የአየር ጥቃት በደረሰበት ወቅት ኖኦን የያዘው የሐማስ አሸባሪ ሲገደል እና እሷም ለህይወቷ አስጊ ያልሆነ ጉዳት አስተናግዳለች። ኖአ ወደ ሺፋ ሆስፒታል ብትወሰድም በሌላ የሐማስ አሸባሪ ተገድላለች።” ብለዋል።
ሐማስ ቀደም ሲል ማርሲያኖ በእስራኤል በተሰነዘረ የአየር ጥቃት መገደሏን ተናግሮ ነበር።
ሃጋሪ መስከረም 26 ማለዳ ላይ የተቀረጸ ነው ያሉትንም ቪዲዮ (ሲሲቲቪ) አሳይተዋል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ወደ ጋዛ ትልቁ እና ዘመናዊው ሆስፒታል ሁለት ታጋቾች ሲገቡ ይታያል።
መስከረም 26 ቀን ባለበት ቪዲዮም የታጠቁ ሰዎች ይታያሉ። አንደኛው ታጋች እየታገለ ይመስላል ። ሌላኛው ደግሞ ቃሬዛ ላይ ሆኖ ይታያል።
ሐማስ ከትልቁ የህክምና ማዕከል ስር የማዘዣ ጣብያ ነበረው የሚለውን ጦሩ እንዲያረጋግጥ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል።
በእስራኤል ስለተለቀቀው ቪዲዮ ምላሽ የሰጠው በጋዛ የሚገኘውና በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል።
ሚኒስቴሩ አክሎም በጋዛ ለደረሰው የጤና አገልግሎት መውደም ሙሉ ኃላፊነቱን የምትወስደው እስራኤል ነች ብሏል።
ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ከመሬት በታች 10 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ያለው እና እስከተዘጋ በር ድረስ የተዘረጋ 55 ሜትር ርቀት ያለውን ዋሻ ያሳያል ያለውን ቪዲዮ ለቋል።
ይህም በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ህንጻዎች “ሐማስ ለሽብር መሠረተ ልማቶቹ እና እንቅስቃሴዎቹ መሸፈኛ” መጠቀሙን “በግልጽ የሚያረጋግጥ” ማስረጃ አካል ነው ብሏል።
ጦሩ በቅርቡ ሐማስን በአል-ሺፋ ሆስፒታል ስር ያለውን ዋሻ በማስመሰል በኮምፒውተር ያዘጋጀውን ሰፊ እና ውስብስብ ዋሻ አቅርቦ ነበር። አሁን ያቀረባቸው ማስረጃዎች ግን ቃል ከተገባው አንጻር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም።

ሐማስ አል-ሺፋን ጨምሮ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሆስፒታሎችን የትዕዛዝ ማዕከላት እና የጦር መሳሪያ ማከማቻ አድርጎ እንደተጠቀመባቸው ማስረጃ አለኝ ስትል አሜሪካም ገልጻለች።
እስራኤል በሆስፒታሉ ውስጥ ማዘዣ ጣብያ መኖሩን ለማረጋገጥ የአሜሪካ የስለላ ድርጅትን ብትጠቅስም፤ አሜሪካውያን ‘መገናኛ’ የሚለውን ቃል መጠቀማቸው አነስተኛ ማዘዥያ ጣብያን ሊያመለክት ይችላል ተብሏል።
እስራኤል ተዓማኒነት ያለው ማስረጃ እየገነባች እንደሆነ እና ማስረጃዎችን ባገኘችበት ጊዜም እንደምታቀርብ እየተናገረች ትገኛለች።
የእስራኤል አጋሮች ሐማስን ለማጥፋት ያለመ ነው ያሉትን ወታደራዊ የአጸፋ ዘመቻ ቢደግፉም ጥቃቱ በሠላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በእጅጉ እንዳሳዘናቸው እየገለጹ ይገኛሉ።
በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ከ12 ሺህ በላይ መሆኑን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው ቀርተዋል የሚል ስጋት አለ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደርም በታጋቾቹ ቤተሰቦች ጫና እያረፈበት ነው። በሐማስ የተያዙትን ታጋቾች ለማስፈታት የበለጠ ጥረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል መንግስት ታጋቾችን ለማስፈታት ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም በመጓዝ ኔታንያሁ መኖሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ሠላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከያዙት አቋም ፍንክች የሚሉ አይመስሉም።
የጦርነቱ የመጀመሪያ ዓላማ ሃማስን ማጥፋት ነው ብለዋል። ሁለተኛው ታጋቾችን ማስመለስ ሲሆን እና ሦስተኛው ደግሞ የጋዛን ስጋት ማስወገድ መሆኑን ተናግረዋል።
