
ከ 6 ሰአት በፊት
በኬንያ ያለው ሥራ አጥነት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በጀርመን ለኬንያውያን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማለማቸውን ተናገሩ።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ለቡድን 20 አገራት ስብሰባ ወደ አውሮፓ ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ ነው።
በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ሠራተኛን ወደ ውጭ የመላክ ስምምነትን እና በአፍሪካ ያለውን ኢንቨስትመንት ማሳደግን ጨምሮ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድሎችን ለመፈለግ ወደ ጀርመን መዲና በርሊን አቅንተዋል።
ፕሬዚደንት ሩቶ እሑድ ዕለት ባደረጉት ንግግር “ የጀርመን መራሔ መንግሥት ከሦስት ወይም ከአራት ወር በፊት ኬንያ ነበሩ። ዛሬ ምሽት ወደ ጀርመን የማቀናውም 200 ሺህ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ቃል ስለገቡልን ነው።በመሆኑም እነዚህን ዕድሎች ለመከታተል መሄድ አለብኝ” ብለዋል።
በቅርቡ ኬንያንና ናይጄሪያን ጨምሮ በአፍሪካ ጉብኝታቸውን ያደረጉት መራሔ መንግሥት ኦላፍ ስኮልዝ በአህጉሯ በተለይም በማዕድን እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
በኬንያ ዕድሜያቸው ከ18-34 ዓመት ከሚሆናቸው ዜጎች መካከል 40 በመቶ ያህሉ ሥራ አጥ ሲሆኑ፣ በአገሪቷ ያለው ምጣኔ ሃብትም በየዓመቱ ወደ ሥራ የሚቀላቀሉ 800 ሺህ ወጣቶችን ለመያዝ በቂ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንዳልሆነ ይነገራል።
- ቡድን 20 ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረትን አባል አድርጎ ተቀበለ9 መስከረም 2023
- አዲስ አበባ ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎች ሥራ አጥነት አለ?17 ጥቅምት 2023
- ‘በአንድ ወቅት የሚያስደስቱኝ ነገሮች በሙሉ ትርጉም አጡብኝ፣ ከሰዎችም መሸሽ ጀመርኩ’6 ጥቅምት 2023
‘ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ’ በሚል በጀርመን በርሊን እየተካሄደ ያለው ስብሰባ በአፍሪካ እና በቡድን 20 አገራት መካከል ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
በአጠቃላይ 13 የአፍሪካ አገራት የዚህ ፕሮግራም አካል ሲሆኑ እነዚህም ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ አይቮሪ ኮስት ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኒጋል ቶጎ እና ቱኒሲያ ናቸው።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ናይጄሪያን ጨምሮ የሌሎች አፍሪካ አገራት መሪዎች ፕሮግራሙን በእንግድነት እየታደሙ ነው።
መስከረም ወር ላይ ቡድን 20 ታሪካዊ በተባለ ውሳኔ የአፍሪካ ኅብረትን አባል አድርጎ የተቀበለ ሲሆን 55 አባላት ያሉት የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 አባል አገራትን መቀላቀሉ ይታወሳል።
ቡድን 20 በኢንዱስትሪ የበለጸጉ እና ከአዳጊ አገራት የላቀ የምጣኔ ሃብት ዕምርታ ያስመዘገቡ አገራት ስብስብ ነው።
