November 21, 2023 

የ“ፍትሕ መጽሔት” ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዛሬ ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከጠበቆቹ ጋር ቀርቧል ።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ፤ በባለፈው ቀጠሮ ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቆች “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የዐቃቢ ሕግን የይግባኝ ቅሬታ እና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲሰጠን ገጽ አጉድሎ ስለሆነ የተሟላ መልስ መሰጠት ባለመቻላችን፣ መልሳችን እንድናሻሽል ይፈቀድልን” በሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

ዐቃቢ ሕግም በበኩሉ “በዚህ አቤቱታ ላይ እኔም አስተያየት መስጠት አለብኝ” ብሎ ተከራክሯል፡፡

ጠበቆቹም “እኛ ስህተት ሠራ ያልነው ፍርድ ቤትን ነው፡፡ ስህተቱን እንዲያረምም የጠየቅነው ፍርድ ቤቱን ነው፡፡ ከዐቃቢ ሕጋ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ዐቃቢ ሕግ ስለማይመለከተው ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ ሊፈቀድለት አይገባም፤” በሚል ተከራክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም “ዐቃቢ ሕግ አስተያየት ይስጥ ወይስ አይስጥ ብሎ ትእዛዝ ለመስጠት ዳኛ ስለሚጎድል ለህዳር 11/2016 ዓ. ቀጠሮ ስጥተናል፤” ማለቱ ይታወሳል፡፡

በአቶ ሸምሱ ሲርጋጋ የመሀል ዳኝነት (ሰብሳቢነት) በሀፊዝ አባጀማል እና መሀመድ አህመድ የግራና ቀኝ ዳኝነት ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም፣ ከሕግ ውጪ “ዓቃቢ ሕግ አስተያየት መስጠት ይገባዋል” ሲል የሰጠው ትእዛዝ ዛሬ ህዳር 11/2016 ዓ.ም በችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለዚህ ዜና ዘጋቢ እንደተናገረው “የተሰጠው ትእዝዛ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ይሄ የፍርድ ቤቱን ተአማኒነት ገና ከመነሻው ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ነው” ካለ በኋላ፤ “ችሎቱ፣ ዐቃቢ ሕግ የሚጠይቀውን ሕገ-ወጥ ጥያቄ በሙሉ እየተቀበለ የሚሄድ ከሆነ፣ ታዲያ እንዴት ነው ነፃና እውነተኛ ፍትሕ የሚገኘው?” ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችም “ዐቃቢ ሕግ አስተያየት ይስጥ” ተብሎ መታዘዙ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ የዐቃቢ ሕግን አስተያየት ህዳር 30 በቢሮ በኩል ከተቀበለ በኋላ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች ያቀረቡት የመልስ ማሻሻያን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ለታኀሣስ 11/2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡