
ከ 4 ሰአት በፊት
ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ካልተሳኩላት ሁለት ሙከራዎች በኋላ ወታደራዊ የስለላ ሳተላይት በተሳካ ሁኔታ ወደ ህዋ መላኳን አስታወቀች።
ሰሜን ኮሪያ ይህን ያስታወቀችው መስከረም ወር ላይ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ከተገናኙ በኋላ ነው።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ጋር በተገናኙበት ወቅት ሞስኮ ሳተላይቶችን ለፒዮንግያግ እንደምትሰጥ ቃል ገብተው ነበር።
ደቡብ ኮሪያ እስካሁን ሳተላይቱ ሥራ ስለመጀመሩ ባታረጋግጥም፣ ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ድጋፍ አግኝታለች ብላ እንደምታምን ገልጻለች።
ሳተላይቱ መምጠቁን ተከትሎም ከሰሜን ኮሪያ ጋር በአውሮፓውያኑ 2018 ወታደራዊ ውጥረትን ለማርገብ የገቡትን ስምምነት ወደ ጎን በማለት ከአገሪቷ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር የደኅንነት ሥራ ማጠናከር እንደምትጀምር አስታውቃለች።
ማሊንግዮንግ-1 የሚል ስያሜ የተሰጣት ሳተላይቷ፣ በትክክል ወደ ምህዋሯ መግባቷንና ሳተላይቷ ኪም ጆንግ ኡን በተገኙበት መምጠቋን ሰሜን ኮሪያ የመንግሥት ዜና ወኪል (ኬሲኤንኤ) ዘግቧል።
ይህንን ተከትሎም ከኒዩክሌር ሚሳይል ማበልጸግ ጋር በተያያዘ ሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ የጣለው የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም አሜሪካንና ጃፓንን ጨምሮ ሌሎች አገራት ድርጊቱን አውግዘዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ “የባሊስቲክ ሚሳይልን በመጠቀም በሰሜን ኮሪያ የሚደረግ ማንኛውም ሳተላይት ማምጠቅ ከጸጥታው ምክር ቤትን ውሳኔ ጋር የሚጻረር ነው” ብለዋል።
ዋና ጸሐፊው ጨምረውም ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ከማበልጸግ ጉዞዋ እንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋይት ሃውስም እንቅስቃሴውን በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ላይ የተቃጣ አሳፋሪ ጥሰት ነው ያለ ሲሆን፣ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳን በአገራቸው ኦኪናዋ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ አቅጣጫ ሳተላይት መምጠቁን አውግዘዋል።
የጃፓን መንግሥት የኦኪናዋ ነዋሪዎች መጠለያ ውስጥ እንዲገቡም ድንገተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ሳተላይቱ ከተያዘለት እቅድ እና ፒዮንግያንግ ለጃፓን ካሳወቀችው የጊዜ መርሃ ግብር ስምንት ቀናት ቀደም ብሎ የተፈፀመ ነው።
- ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ሳተላይት በጦር መሳሪያ ሊቀያየሩ ነው ተባለ13 መስከረም 2023
- ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለሩሲያ ሰጥታለች ስትል አሜሪካ ከሰሰች14 ጥቅምት 2023
- የሰሜን ኮሪያው መሪ ወደ ሩሲያ በአውሮፕላን መሄድ የፈሩት ለምንድነው?12 መስከረም 2023
ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም ግንቦት እና ነሐሴ ወር ላይ ሙከራ ያደረገች ሲሆን ሁለቱም ሳይሳኩላት ቀርተው ነበር።
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሺዳ ሳተላይት መምጠቁን አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን የባሊስቲክ ሚሳይል ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ሳተላይት ማምጠቅ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔን በግልጽ የጣሰ ነው ሲሉ ኮንነውታል።
“ለሕዝባችን ደኅነንት ትልቅ ስጋት የሆነ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኬሲኤንኤ የሰሜን ኮሪያን የህዋ ምርምር ተቋም ጠቅሶ እንደዘገበው ሳተላይቱ የመጠቀው ከቻይና ጋር በሚያዋስነው ሰሜን ምዕራብ ከሚገኘው ሶሄ የሳተላይት ማምጠቂያ ጣቢያ ነው።
ሰሜን ኮሪያ በስኬት አምጥቄዋለሁ ያለችው የስለላ ሳተላይት ስለመሆኑ አልተረጋገጠም።
ሮኬቱ የስለላ ሳተላይት መሆኑ ከተረጋገጠ ግን በዚህ ዓመት በሰሜን ኮሪያ የተደረገው ሦስተኛ ሙከራ ይሆናል።
የስለላ ሳተላይቱ ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆን ኡን በቀጣይ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከታተል እና የራሳቸውን ኢላማ በትክክል ለመምታት ይረዳቸዋል ተብሏል።
ይህ ሴኡል በ2025 አሳካዋለሁ ካለችው አምስት የስለላ ሳተላይቶች የመጀመሪያው እንደሆነም ተዘግቧል።
