አብይ አህመድ ባላፈው የታላቁ ሩጫ ላይ የሚለበሰው ቲሸርት ሶስቱን የኢትዮጵያ ቀለማት እንዳያንጸባርቅ መመሪያ ሰጥቷል። ( አንዳርጋቸው ፅጌ)
ከሳምንታት በፊት የደረሰኝ መረጃ ነው። ስለ መረጃው ትክክለኛነት ምንም ጥርጣሬ የለኝም። መረጃው እንደደረሰኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ውስኜ ነበር። ሆኖም ግን ስንት ከዚህ የባሰ ጉዳይ እያለ ለምን ጊዜዬን አጠፋለሁ ብዬ ተውኩት።
ሆኖም ግን እስከትናንትና ማታ ድረስ ብዙም ትኩረት ያልሰጠኋት አንዲት የመንግስት ካድሬ ሳትሆን እንዳልቀረች የገመትኳት ሴት፣ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ በትዊተር ገጿ ላይ የጻፈችው ማስተባበያ ስላስገረመኝ የሆነ ነገር ለማለት ወሰንኩ። የሰጠችው ማስተባበያ ዘሃበሻ የተባለው የዩትዩብ ቻናል የፈጠራ ወሬ አሰራጭቷል ከሚል ክስ ጋርም ጭምር ነው።
እንዳጋጣሚ ሆኖ ይቺው ሴት በትናንትና እለት ይመስለኛል የአህያ ፊት ላይ የኔን የፊት ምስል ለጥፋ ፖስት አድርጋ ጓደኞቼ ልከውልኝ አይቼ በጣም አስቆኝ አልፌው ነበር። የዛሬ መልእከቴ በዛ ምክንያት ግን የተጻፈ አይደለም። ይህ ጽሁፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ነውረኛነት ለማሳየት ተጨማሪ ግብአት ሆኖ ስለሚያገለግል ብቻ ነው የጻፍኩት።
በሌላ በኩል ቢታዩትም እሷ የምትለጥፈውን ነገር እየተከታተልኩ ምላሽ መስጠት ከአቅሜ በላይ ነው። ይች ሴት ከትዊተር አካዎንቷ እንደተረዳሁት 29300 ጊዜ ፖስት አድርጋለች። እኔ ደግሞ እስከዛሬ ፖስት ያደረሁት 188 ብቻ ነው። እሷ ድስቷ ትዊተር ነው። እንዲህ ትዊተር ላይ ተጥዳ ውላ ከምታድር ሴት ጋር አፍ መካፈት እንደማይቻል ሰለማውቅ ሰራ ፈትቼ እንዲህ አይነቱን እሰጣ ገባ እንደማልሞክረው ወዳጆቼ ያውቃሉ።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከሳምንታት በፊት ያገኘሁት መረጃ በቀጥታ የሚለው ከጠቅላይ ሚስቴር ቢሮ በተሰጠ መመሪያ በታላቁ ሩጫ ላይ የሚለበሰው ቲሸርት ሶስቱን የኢትዮጵያ ቀላማት እንዳያንጸባርቅ ተደርጓል የሚል ነው። መረጃውን ዝም ብዬ አልተቀበልኩም።
ይህ መመሪያ ለማን ነው የተሰጠው የሚል ጥያቄ አቅርቤያለሁ። ያገኘሁት መልስ መመሪያው የተሰጠው “ከታላቁ ሩጫ ጋር በተያያዘ ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ከፊደራል ፖሊስ፣ ከአዲአበባ ፖሊስና ከሃገር ደህንነት ተወጣጥቶ ለቆመው ግብረ ሃይል ነው” ተብያለሁ። ይህ ግብረ ሃይል ደግሞ ሃይሌ ገብረስላሴን በአካል አግኝቶ በታላቁ ሩጫ የሚለበሰው ቲሸርት ሶስትቱን ቀላማት በአንድ ላይ እንዳይዝ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ትእዛዝ መውረዱን እንደነገረው ተነግሮኛል።
በሩጫው ቀን ቲሸርቱ በትእዛዝ ቀይ ቀለም የሌለበት አረንጓዴና ቢጫ ቀለማት ብቻ ያለው ሆኖ አይተነዋል። አልፎ አልፎ ቀይ ቀለም ቢታይም ሯጮቹ ከለበሱት ሱሪና ቁምጣ ላይ እንጂ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ያቀረቡት ቲሸርት አልነበረም።
ታልቁ ሩጫ በተደረገበት ቀን የሃይሌን ምስል በዩትዩብ ስመለከት አዝኜለት ነበር። በአለም የስፖርት አደባባይ ባሸነፈ ቁጥር የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዞ በደስታ እንደሚፈነድቅ ሜዳሊያ ሲሸለምና ሰንድቋ ስትሰቀል በስሜት እንዴት እንደሚያለቅስ እናውቃለን። ለዚህ ሰው የምታዘጋጀው ቲሸርት ሶስቱን ቀለማት መያዝ የለበትም ተብሎ በሰላምና ደህንነት ግብረ ሃይሉ ሲነገረው ምን ተሰምቶት ይሆን፣ በማለት ነው ለሃይሌ ያዘንኩት።
እኔ የዘሃበሻ ደጋፊ አይደለሁም። በቅርቡ ከኔ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭቶ ደውዬ እንዲያስተካክል ነግሬዋለሁ። የተሰተካከለውን አላየሁትም። አደርጋለሁ ስላለኝ ያደርገዋል ብዬ ትቼዋለሁ። በታላቁ ሩጫ ላይ ስለነበረው የቀለም አመራረጥ ላይ ግን ዘሃበሻ ያወጣው መረጃ ትክክልና ምንም ስህተት የሌለበት ነው።
ሴትየዋ የዘሃበሻን መረጃ ለማስተባበል እዚህና እዚያ ቀይ ቀለሞችን የሚያሳዩ በሩጫው ወቅት የተነሱና በሩጫው ወቅት ፍጽሞ ያልነበሩ የቆዩ ፍቶግራፎችን ብትለጥፍም እንደጎርፍ ሲነጉድ የነበረው ሯጭ በአረንጓዴና በቢጫ ቀለም ከተሰራ ቲሸርት ውጭ ሌላ ቲ ሸርት እንደለበሰ ማስረጃ አይሆንም።
በዙህ አጋጣሚ ይች ሴት ሳታውቀው ይህን ማስተባበያ እንድትጽፍ መመሪያ የሰጣት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ወይም ጠቅላይ ሚስትሩ ራሱ ለመሆኑ ተጨማሪ መረጃ ሰጥታናለች። በዚህም ከጠቅላዩ ጋራ አንድ አልጋ ተጋሪ፣ በእንግሊዝኛው “bed fellow” መሆኗን አሳይታናለች። ለ Bedfellow ሌላ ትርጉም እንዳትሰጡብኝ በእንግሊዝኛው ትርጉሙ ነው የተጠቀምኩት የቅርብ ሰው የሚለውን።
ሴትየዋ ዘሃባሻን የሃስት መረጃ አሰራጭቷል ብቻ ሳይሆን ወርቁ አይተነው ከተባለ ባለሃብት ገንዝብ ይቀበላል የሚል ክስ መሰል ነገር አቅርባበታለች። ወርቁ አይተነው አማራ ነው። ለምን ከዘሃበሻ ባቀረበው እወነተኛ ሆኖም ግን ሴትየዋ የተሳሳተ ካላችው መረጃ ጋር አቶ ወርቁ ስሙ እንዲጠቀስ ተፈለገ? ማነው የፈለገው? እነዚህ ጥያቄዎች መልሰው ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይወስዱናል።
“ወርቁ አይተነው ለዘሃበሻና ለአንድ ሌላ ሚድያ ገንዝብ እንደሚሰጥ እናውቃለን” የሚለውን ንግግር እኔም ከጠቅላዩ ጋራ አንድ አልጋ ተጋሪ (bed fellow) የቅርብ ሰው በነበርኩበት ዘመን ከአንደበቱ ሰምቼዋለሁና።
በመጨረሻም በየባእላቱ ከእናቶች የነጠላና የቀሚስ ጥለት ላይ የሚታይን፣ እግዜር ከፈጠራቸው ሰባት ዋና ቀለሞች ሶስቱን ለመቅደድ ወታደር የሚያሰማራ በሽተኛ አገዛዝ በታላቁ ሩጫ ቲሸርት ላይ ሶስቱን ህብረ ቀለማት በአንድ ላይ እንዳይከሰቱ የሚል ትእዛዝ ቢሰጥ ለምን እንገረማለን። በተጫባጭም ትእዛዝ ተሰጥቷል። ትእዛዙን የተቀበሉት፣ ያስተላለፉትና የተገበሩት ያውቁታል። ( አንዳርጋቸው ፅጌ)
