

ቀን:
የትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎች ምዘናና የክፍል ዝውውር ረቂቅ መመርያ፣ አንዲት የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪ ከ15 ቀናት በላይ በወሊድ ምክንያት ከትምህርቷ የምትቀር ከሆነ በዚያው የትምህርት ዘመን ትምህርቷን መቀጠል እንደማትችል ደነገገ፡፡ተማሪዋ ለ15 ተከታታይ ቀናት በወሊድ ምክንያት የምታርፍ ከሆነ ትምህርቷን መቀጠል እንደማትችል የሚገልጸው ረቂቅ መመርያ፣ ለ16 ቀናትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት የምትቀር ከሆነ በዚያ ዓመት ስትከታተል ከነበረው ትምህርት የምትታገድ መሆኑን ያስረዳል፡፡ሆኖም ተማሪዋ በቀጣዩ ዓመት ትምህርቷን መቀጠል የምትፈልግ ከሆነ፣ ‹‹ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› መቀጠል እንደምትችል ይፈቅዳል፡፡የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችን (1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል) ያሉ ተማሪዎች ከክፍል ክፍል የሚዘዋወሩበትን አሠራር በዝርዝር የሚያስረዳው መመርያው፣ ማንኛውም ተማሪ በአንድ የትምህርት ዘመን ለ12 ቀናት ከትምህርት ገበታው የሚቀር ከሆነ ትምህርቱን እንዳይቀጥል እንደሚደረግ ይገልጻል፡፡በተጨማሪም ስለየተፋጠነ የተማሪዎች የክፍል ክፍል ዝውውር የሚደነግገው የመመርያው ክፍል እንደሚያስቀምጠው፣ አንድ ተማሪ ከፍተኛ ውጤት ካመጣ ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ቀጣይ ሊዘዋወር ይችላል፡፡ይህ አሠራር ተግባራዊነቱ በሦስተኛ፣ በአራተኛና በዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ብቻ መሆኑ በመመርያው ተመልክቷል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ የሚታቀፉ ተማሪዎች በመጀመሪያው የመንፈቅ ዓመት ውጤታቸው፣ በአማካይ ከ95 በመቶ ያነሰና በሁሉም ትምህርት ዓይነቶች ቢያንስ ከ90 በመቶ በታች ውጤት ማምጣት እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡ተማሪዎቹ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በሚያመጡት ውጤት ተመርኩዘው በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ቀጣይ ክፍል ለመዘወዋወር፣ ‹‹በቅድሚያ የተማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ስምምነት›› ሊኖር እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡በመጀመርያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (የስድስተኛና የስምንተኛ ከፍል ክልላዊ ተፈታኞችን ጨምሮ)፣ በሁሉም ትምህርት ዓይነቶች በአማካይ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ሲያመጡ ነው ተማሪዎች ወደ ቀጣይ ከፍል የሚዘዋወሩት፡፡ በተለይ በዋነኛ የትምህርት ዓይነቶች ከ50 በመቶ በታች ያመጣ ተማሪ ግን ወደ ቀጣይ ክፍል አይዘዋወርም ይላል መመርያው፡፡ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ለ14 ዓመታት ትምህርቱን ሲከታተል የቆየ ተማሪ፣ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገባው ትምህርት ሚኒስቴር የሚያስቀምጠውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ ሲያሟላና ዋነኛ የትምህርት ዓይነት ተብለው በሚመደቡት ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ሲያመጣ ነው፡፡ረቂቅ መመርያውን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
