

ኪንና ባህል የሕፃናት ቀን በአገር ፍቅር ቴአትር
ቀን: November 22, 2023
በዳንኤል ንጉሴ
የሕፃናት ቀንን አስመልክቶ መንግሥታዊና መንሥታዊ ያልሆኑ አካላት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ ሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንትም የሕፃናት ቀንን ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በአገር ፍቅር ቴአትር በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡
በዝግጅቱ ሕፃናት የተለያዩ ትዕይንቶችን አሳይተዋል፡፡ የማርሽ ባንድ፣ ባህላዊ ውዝዋዜ፣ ሰርከስ፣ ግጥም፣ ለባለተሰጥኦ ልጆች ሽልማት የፕሮግራሙ ክፍሎች ነበሩ።
የሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ባለቤት አቶ ጌታቸው ዓለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮግራሙ ሕፃናት ተሰጥኦዎቻቸውን የሚያወጡበት፣ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ ትንሿን ኢትዮጵያ የሚያዩበት፣ አብሮ የመኖር ባህልን የሚያውቁበትና የኢትዮጵያውያንን እሴቶች የሚገነዘቡበት ነው፡፡
ሰምና ወርቅ መሰል ፕሮግራም መሥራት የጀመረው ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ፕሮግራሙ ወርኃዊ እንደነበር፣ የሕፃናት መዝናኛና ቁምነገር ፕሮግራም በሚል ዓላማ በየወሩ የመጀመሪያ እሑድ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተከናውኖ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡
ከዝግጅቱ ዋና ዓላማ አንዱ የባለተሰጥኦ ሕፃናት ሽልማት ፕሮግራም መሆኑንና በቀጣይ በአዲስ አበባ ያሉ ሕፃናትን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ባለተሰጥኦ ሕፃናትን በማምጣት የመሸለም ዕቅዶች እንዳላቸው አክለዋል።
ሕፃናትን የመሸለሚያ የተለያዩ የመለያ መደቦች ተዘጋጅተዋል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በአገር በቀል እውቀት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርምር ሥራ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሁም ስነፈለግ ላይ የሚሠሩ ሕፃናት ባሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እውቅና በመስጠት ሌላ ተጨማሪ ጎበዝና ተስፋ ያላቸውን ሕፃናት ማነቃቃት ሥራቸው እንደሆነና መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አብረዋቸው እንዲሠሩ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
