አደጋው የደረሰበት ቦታ ፖሊሶች ቆመው

ከ 4 ሰአት በፊት

በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር በኒያጋራ ፏፏቴ አቅራቢያ በሚገኝ ድልድይ ላይ በመኪና ላይ ያጋጠመው ፍንዳታ የሽብር ጥቃት ስለመሆኑ የሚያሳይ ምልክት አለመኖሩን የኒው ዮርክ ገዢ ተናገሩ።

ተሽከርካሪው በፍተሻ ጣቢያው ላይ ተጋጭቶ በእሳት የተያያዘው ከኒው ዮርክ ኒያጋራ ፏፏቴ ወደ ሬንቦው ድልድይ በፍጥነት እየተጓዘ ሳለ ነበር።

ረቡዕ ጠዋት ላይ ባጋጠመው በዚህ አደጋ በመኪናው ውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ የአሜሪካ የድንበር ጠባቂም ጉዳት ደርሶበታል።

አደጋውን ተከትሎም ድልድዩ እንዲሁም በቀጠናው ያሉ ሌሎች ሦስት የድንበር መሻገሪያዎች ተዘግተው ነበር።

ከአሜሪካ በኩል ወደ ካናዳ ለመሻገር ሰነዶቻቸውን ለማሳየት ከመኪናቸው ወርደው ድልድዩን በእግራቸው ካቋረጡ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ዶር ታማንግ የተባለ የቶሮንቶ ነዋሪ፣ ፍንዳታው ሲያጋጥም በአሜሪካ ገቢዎች እና ድንበር ጥበቃ ሕንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

የዓይን እማኙ በሕንጻው ውስጥ ሆኖ መሬቱ ሲርድ ተሰምቶኛል ብሏል።

ከዚያም ወዲያውኑ የድንበር ጠባቂ መኮንኖች ለደኅነንት ሲባል ወደ ካናዳ በኩል እንድንሆን ነገሩን በማለት ወደ መኪናው ተመልሶ ለመሄድም ከስምንት ሰዓት በላይ ለመጠበቅ መገደዱን ገልጿል።

አደጋው የተከሰተው በዓመቱ እንቅስቃሴ ከበዛባቸው ቀናት አንዱ በሆነውና በአሜሪካ በስፋት የሚከበረው የምስጋና በዓል ዋዜማ ላይ ነበር።

የኒውዮርኳ ገዢ ካቲ ሆቹል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከአደጋው ጋር በተያያዘ የሽብር እንቅስቃሴ እንዳለ የሚያሳይ ምልክት የለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ አሽከርካሪው ሆነ ብሎ መኪናውን በፍተሻው ጣቢያ ላይ አጋጭቶት ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ብለዋል ገዢዋ።

መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት ሲጓዝ እንደነበር የተናገሩት ሆቹል፣2.4 ሜትር ከፍታ ያለውን አጥር ዘሎ ገብቷል ብለዋል።

እንደ ገዢዋ መግለጫ ከሆነ ተሽከርካሪው ከሞተሩ በስተቀር ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን የታርጋ ቁጥሩም አልተገኘም።

በኒያጋራ ፏፏቴ መታሰቢያ የሕክምና ማዕከል የሕዝብ ደኅንነት እና ድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር የሆኑት ጄምስ ሱተር ፣ አንድ ወንድ ታማሚ በድንገተኛ ክፍል ሕክምና እየተደረገለት እንደሆነና ያጋጠመው ጉዳት ለሕይወቱ አስጊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ገዢዋ ግለሰቡ የአሜሪካ ገቢዎች እና ድንበር ጥበቃ መኮንን ነው ብለዋል።

ገዢዋ ጨምረውም ወደ ኒውዮርክ የሚያስገቡ ሁሉንም መግቢያዎች ለመከታተል የኒው ዮርክ ግዛት ፖሊስ ከአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ የሽብር ግብረ ኃይል ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ መንገደኞች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲጓዙ መንግሥታቸው ከአሜሪካ ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም በአገሪቷ በሚገኙ ድንበሮች ላይ ተጨማሪ የጸጥታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፣ ክስተቱን ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።

ለምስጋና በዓል ማሳቹሴትስ ያሉት ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም ስለ አደጋው ገለጻ እንደተደረገላቸው ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

አደጋው የደረሰበት ‘ሬንቦው’ ድልድይ ኦንታሪዮን ከኒው ዮርክ ጋር እንዲሁም የአሜሪካ ከተማ ኒያጋራ ፎልስን ከካናዳው ኒያጋራ ፏፏቴ ጋር የሚያገናኝ ነው።