ስቱዋርት ሼልድዊዝ

ከ 4 ሰአት በፊት

በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን የውጪ ጉዳይ ረዳት የነበሩት ባለስልጣን በጋዛ የደረሰውን የፍልስጤማውያንን ግድያ በመደገፍ እና የእስልምና እምነትን በማንቋሸሸቻው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ፖለቲከኛው ኒውዮርክ ውስጥ አንድ የምግብ ነጋዴ ላይ ነው በሺዎች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ህጻናት በቂ አይደለም እንዲሁም ሌሎች ስድቦችን የሰነዘሩት።

ስቱዋርት ሼልድዊዝ የተባሉት የቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣን በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ በሆነ አንድ ቪዲዮ ላይ ነጋዴውን “አሸባሪ” ሲሉ ይታያሉ። ከክስተቱ በኋላ በሰጡት ቃለመጠይቅ በቪዲዮ ላይ የሚታዩት ሰው እሳቸው እንደሆኑ አምነዋል።

ሰውዬው ይህንን ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ ነጋዴው ሃማስን የሚደግፍ ቃላት በመጠቅም ለጸብ ጋብዦኛል ብለዋል።

ሞሀመድ ሁሴን ‘ሃላል’ ምግቦችን በኒውዮርክ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የሚሸጥ ሲሆን ሃማስን የሚደግፍ አስተያየት አልሰጠሁም ብሏል።

የኒውዮርክ ፖሊስ ቃለ አቀባይ ከዚህ ክስተት በኋላ የቀድሞው ባለስልጣን ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን አረጋግጦ የክሱ ዝርዝር ግን ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ከባለስልጣኑ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆኑ ቪዲዮዎች ከአንድ በላይ ሲሆኑ በቀን ውስጥ በተለያየ ጊዜ የተቀረጸ ነው።

በአንደኛው ቪዲዮ “ታውቃለህ? 4 ሺህ የፍልስጤም ህጸናት ገድለን ከሆነ ፣ ያ በቂ አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ።

የኤክስ ወይም በመደበኛ ስሙ ትዊተር መረጃ እንደሚያሳየው 40 ሚሊዮን ጊዜ በታየ ሌላ ቪዲዮ ደግሞ ነጋዴውን ከመዝለፍ አልፈው እጅግ ጸብ ጫሪ ንግግሮችን በነብዩ መሀመድና ቁርአን ላይ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ነገሩን ሲታዘብ የነበረ ሌላ ሰው “ሰውዬው ላይ በደል እያደረስክ ነው” ሲል ተሰምቷል።

ይህንን ዘለፋ ያደረሱት ስቱዋርት ሼልድዊዝ የእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይን የሚከታተለውን ጽህፈት ቤት ጨምሮ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ አገልግሎት አላቸው። ።

በተጨማሪም የኋይት ሃውስ ብሄራዊ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆነው በኦባማ አስተዳደር ወቅት ሰርተዋል።

ስውዬው ዘ ዴይሊ ቢስት ለተባለ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት በቨዲዮ ላይ የሚታዩት እሳቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

“አሸባሪነትንና የንጹሃን ግድያን የሚቀበል ሰው ለሚሰጠው አስተያየት ምላሽ ያስፈልጋል” ማለታቸውም ተነግሯል።

በሌላ ሚዲያ ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ደግሞ “ይህ ነገር በመፈጠሩ ተጸጽቻለሁ። አዝናለሁ። ነገር ግን ነገሩ በጣም በተካረረበት ሰዓት ማለት የሌለብኝ ነገር ብዬ ሊሆን ይችላል” ማለታቸው ተዘግቧል።

ከዚህ ክስተት በኋላ በርካቶች የቀድሞ ባለስልጣን ስድብ፣ ዘለፋ እና ማስፈራሪያ ሰለባ ለሆነው ነጋዴ በርካቶች ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የኒው ዮርክ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ በኤክስ ገጻቸው “ሙስሊም ጠልነት ጥላቻ ነው። ይህ አይነቱ ክብረነክ ሁኔታ በከተማችን ቦታ የለውም። እናወግዘዋለን። በዚህ ሁኔታ ብቻችንን እንዳልሆንን ስናይ ደግሞ እንደሰታለን” ብለዋል።

ነጋዴው ሁሴን የተውልደ ሀገሩ ግብጽ ሲሆን ለኒውዮርክ ፓስት በሰጠው አስተያት ዘለፋ እና ማስፈራሪያ ያደረሱበትን የቀድሞ ባለስልጣን ላይ ክስ የመመስረት ሃሳብ እንዳለው ተናግሯል።