የእንባ ጠባቂ ተቋም እና የኢቢሲ አርማዎች

23 ህዳር 2023, 15:53 EAT

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መንግሥታዊው የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የዘገባ ሽፋን እንደነፈገው በመግለጽ ማብራሪያ ሲጠይቅ፣ ኢቢሲ በበኩሉ ዘገባዎቹን የሚሠራው ጉዳዮች ምን ያህል ለዜና የሚመጥኑ መሆናቸው መሠረት አድርጎ መሆኑን ገለጸ።

መንግሥታዊው የአስተዳደር በደል መርማሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ላቀረበው ቅሬታ ምክንያት የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋሙን በተመለከተ ያጸደቀው አዋጅ ነው።

በዕለቱ ምክር ቤቱ ይህንን አዋጅ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ ኢቢሲ “ምንም ሳይል እንደዘለለው” በመግለጽ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ለመገናኛ ብዙኃኑ በደብዳቤ ማብራሪያ መጠየቁን የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 11/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ያጸደቀው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የማቋቋሚያ አዋጅ ለተቋሙ ተጨማሪ ሥልጣን እና መብት የሰጠ ነው።

ከዚህ በፊት የአስተዳደራዊ በደል ምርመራ ሥራው በመንግሥት ተቋማት ብቻ ተወስኖ የነበረው የዕንባ ጠባቂ መሥሪያ ቤት፤ በአዲሱ አዋጅ በግል ተቋማት ውስጥም ምርመራ እንዲያደርግ ሥልጣን ሰጥቶታል። በተጨማሪም አዲሱ አዋጅ ለተቋሙ ተሿሚዎች እና መርማሪዎች ያለመከሰስ እንዲሁም ያለመታሰር መብት የሰጠ ነው።

ይህ አዋጅ በጸደቀበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የኢቢሲ ሠራተኞች የአስተዳደር ደንብም በተመሳሳይ ጸድቋል። ኢቢሲ በዕለቱ ባስተላለፈው ዘገባ ስለ ሠራተኞቹ አስተዳደር ደንብ የዘገባ ሽፋን ቢሰጠም፣ የዕንባ ጠባቂ ተቋምን አዋጅ በተመለከተ ግን “ምንም ሳይል” ማለፉን በተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ የተፈረመው ደብዳቤ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይፋዊ የዩቲዩብ ገጽ ላይ በዕለቱ የተላለፈው የቀን ሰባት ሰዓት ዜና፤ ለኢቢሲ ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ የአምስት ደቂቃ ገደማ የዘገባ ሽፋን ተሰጥቶታል። በዕለቱ የምሽት አንድ ሰዓት ዜና ላይም ይህ ደንብ በድጋሚ ሽፋን ያገኘ ሲሆን የዕንባ ጠባቂ ተቋም አዋጅ መጽደቅን በተመለከተ ግን በሁለቱም የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ላይ የተካተተ ዘገባ የለም።

ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ

ኢቢሲ “የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን” መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ፤ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች እና የሚወጡ አዋጆችን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ አለበት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ሁኔታም የኢቢሲ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ “ተነጥሎ” ሽፋን ማግኘቱ ተገቢ እንዳልሆነ አክለዋል። ይህ የዶ/ር እንዳለ ሀሳብም ተቋሙ ለኢቢሲ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተንጸባርቋል።

የአዋጅ ማሻሻያው የተቋሙን የምርመራ ወሰን ያሰፋ መሆኑን የጠቀሰው ደብዳቤው፤ “ጉዳዩ ለምን ሽፋን እንዳልተሰጠው ምክንያቱን መገመት እንኳን በእጅጉ አስቸጋሪ ነው” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

“[የአዋጁ መጽደቅ] የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ስለሆነ፤ አንዱን ዘግቦ ሌላውን መዝለል ለሕዝብ እና ለምክር ቤቱ ሙሉ ሥራዎች ዕውቅና አለመስጠት ነው ብለን እናምናለን” ሲልም ተችቷል።

ኢቢሲ የዘገባ ሽፋን ያልሰጠበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነለት በደብዳቤው የገለጸው ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ፤ መገናኛ ብዙኃኑ “ለምን [የዘገባ] ሽፋን እንደከለከለው” ማብራሪያ እንዲሰጠውም ጠይቋል።

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ያወጣቸውን “በርካታ” መግለጫዎች ለኢቢሲ ቢልክም የዘገባ ሽፋን አለማግኘታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ዶ/ር እንዳለ፤ አዲሱን አዋጅ በተመለከተ ግን “[የመገናኛ ብዙኃኑ] ያላስተላለፈበትን ምክንያት ከእኛ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አንጻር ‘እንዲህ ነው’ የሚል ነገር ያምጣልን ከዚያ በኋላ በተጨማሪ የምንወስደው እርምጃ ይኖራል” ሲሉ የመሥሪያ ቤቱን አቋም አስታውቀዋል።

የእንባ ጠባቂ ተቋም ያቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላልኝ መለሰ፤ ደብዳቤው እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኢቢሲ አንድን ጉዳይ የሚዘግበው አስቀድሞ ጉዳዩን ተመልክቶ ሽፋን ለመስጠት ከወሰነ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

“[ለኢቢሲ] የቀረበ የሚዲያ ሽፋን ጥያቄ በሙሉ ይሸፈናል ማለት አይደለም። ለዜና የሚመጥን መሆኑ ይታያል፤ እንደገናም ደግሞ ኤዲቶሪያል ኮንፈረንስ ነው ‘ይህንን ዜና እንዘግብ አንዘግብ’ የሚለውን የሚወስነው” ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋሙ የሚከተለውን አሰራር አስረድተዋል።