ከተከሳሾቹ መካከል ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ
የምስሉ መግለጫ,ከተከሳሾቹ መካከል ገነት አስማማው፣ ዳዊት በጋሻው እና መስከረም አበራ

22 ህዳር 2023

አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ጨምሮ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 23 ተከሰሳሾች ካቀረቧቸው አራት የክስ መቃወሚያዎች ውስጥ ሦስቱ በፍርድ ቤት ውድቅ ሲደረጉ፣ ተከሳሾች በዝርዝር የፍሬ ነገር ጉዳይ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ደግሞ ተቀባይነት አገኘ።

ተከሳሾቹን መቃወሚያ ውድቅ ያደረገው ዛሬ ረቡዕ ኀዳር 12/2016 ዓ.ም. የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ በሕገ መንግስት ጉዳዮች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው የተከሳሽ ጠበቆች በጽሁፍ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ እና የዐቃቤ ሕግን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር።

ጠበቆች በ10 ገጾች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው ክስ “የፖለቲካ አጀንዳ የያዘ” መሆኑን በመጥቀስ ክሱ ወድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። የተከሳሽ ጠበቆች ክሱን የተቃወሙት አራት ጉዳዮችን በማንሳት መሆኑን ከተከሳሾቹ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቆቹ በክስ መቃወሚያቸው ያነሱት ቀዳሚው ነገር “አንደኛ የተከሰስንበት ጉዳይ የሽብርን ሕግ የሚያሟላ አይደለም በአገራችን ሕግ መሠረት ሽብር ተብሎ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟላ አይደለም” የሚል መሆኑን ጠበቃ ሄኖከ ገልጸዋል።

ቢቢሲ በተመለከተው የክስ መቃወሚያ ላይ ጠበቆች በዐቃቤ ሕግ ክስ ላይ፤ “የፖለቲካ እና ርዕዮተ ዓለም ግባቸውን በኃይል ለመጫን [ተንቀሳቅሰዋል]” በሚል የቀረበባቸውን ውንጅላ ተቃውመዋል።

ይህ የዐቃቤ ሕግ ክስ በጠበቆች ተቃውሞ የደረሰበት፤ “የትኛውን ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ለመቀየር እንደታሰበ በክሱ ላይ በግለጽ መጠቀስ ይኖርበታል” በሚል ነው።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለመቃወሚያው በሰጠው የጽሁፍ ምላሽ ተከሳሾች ያቀረቧቸው ክርክሮች “የተከሰሱበትን ሕግ እና የቀረበባቸውን ክስ በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ነው” ብሏል።

የግራ ቀኙን መከራከሪያ የመረመረው ችሎቱ “እናንተ ልትጭኑት ወይም በኃይል ልታስፈጽሙት ያቀዳችሁት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተብሎ የታሰበው ‘የአማራ ሕዝብ ርስት አና ግዛቶች ተወስደውበታል እና በኃይል መመለስ አለባቸው፣ የአማራ ሕዝብ ተበድሏል የሚሉ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ እንደተገነዘበ ገልጾ በተከሳሾች በኩል ያቀረበነውን መቃወሚያ ሳይቀበለው ቀርቷል” ሲሉ አቶ ሄኖክ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“[ክሱ] አዲስ ስም የማጥፋት ትርክት ማስጀመሪያ እና የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸም የቀረበ [ነው]” የሚለው ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገው እና በጠበቆች የቀረበው ሌላኛው የክስ መቃወሚያ ነው።

ጠበቆች በመቃወሚያቸው “የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ የቀረበው ክስ ውድቅ እንዲደረግለን እንጠይቃለን” ብለዋል።

ዛሬ ረቡዐ ረፋድ በሁለት ዳኞች የተሰየመው ችሎቱ፤ “እነዚህ ነጥቦች በቀጠይ ማስረጃ በሚሰማበት ጊዜ [የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸም የቀረበ] ነው አይደለም የሚለው በማስረጃ የሚለይ ነው እንጂ አሁን ባለው ደረጃ በመቃወሚያ የሚወሰን አይደለም” በሚል ውድቅ ማድረጉን ጠበቃ ሄኖክ አመልክተዋል።

በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ያገኘው እና ሌላኛው የክስ መቃወሚያ ዝርዝር የፍሬ ነገሮች ጉዳይን የተመለከተ ነው። ጠበቆች በክስ መቃወሚያቸው ላይ “ወንጀሉ የተፈጸመበት ጊዜ እና ስፍራ፣ የተበደለው ሰው ስም፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት ንብረት በክሱ ላይ በግልጽ መቅረብ አለበት” ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በመሠረተው ክስ ተከሳሾች ፈጽመውታል ባለው “ድርጊት” 217 ሰዎች ላይ የሞት 297 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሎ ነበር። በተጨማሪም 1.29 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ውድመት መድረሱንም ዐቃቤ ሕግ ገልጾ ነበር።

ጠበቆች ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ደረሱ በሚል ያሰፈራቸው የጉዳት አይነቶች እና መጠኖች በክሱ ላይ በግልጽ መቅረብ ይገባቸዋል የሚል መቃወሚያ አቅርበዋል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ማስቀመጥ፤ “ክሱን የሚያንዛዛ እና ለፍትህ መስጠት አደናቃፊ ይሆናል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ ይህን ቢልም ፍርድ ቤቱ በበኩሉ “ዐቃቤ ሕግ የደረሰውን ጉዳት አጠቃልሎ፣ አሻሽሎ ሊያቀርብ ይገባል” የሚል ብያኔ መስጠቱን ጠበቃ ሄኖክ ጠቁመዋል።

የዛሬው የችሎት ውሎ ከመጠናቀቁ በፊት በቀጣይ ቀጠሮ “ዐቃቤ ሕግ የተጠቀሱትን ፍሬ ነገሮች በክሱ ላይ አጠቃልሎ እና አሻሽሎ እንዲቀርብ” ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠበቃው አክለዋል።

በዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ ስም በሚጠራው መዝገብ ላይ ክስ የተመሰረተባቸው 51 ግለሰቦች ቢሆኑም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ግን 23ቱ ብቻ ናቸው።

በቃሊቲ እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙት 23ቱም ተከሳሾች ዛሬ በችሎት በአካል ተገኝተው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል። ከ23 ተከሳሾች መካከል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ መስከረም አበራ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው እና ገነት አስማማው ይገኙበታል።