ሊ ዮንግ ሱ የተባሉ የ95 ዓመት ተሟጋች እና ሰለባ

ከ 4 ሰአት በፊት

ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በወታደራዊ የወሲብ ንግድ ቤቶች ውስጥ እንዲሰሩ አስገድዳቸዋለች ለተባሉ ሴቶች ካሳ እንድትከፍል ተወሰነባት።

ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የደቡብ ኮሪያው ፍርድ ቤት ነው።

ለጃፓን ወታደሮች ሲባል ለወሲብ ባርነት ተዳርገዋል የተባሉ 16 ሴቶች ቀደም ሲል ጉዳያቸው ውድቅ ተደርጎ ነበር።

በደቡብ ኮሪያዋ መዲና ሴኡል በሚገኝ የአውራጃ ፍርድ ቤትም በአውሮፓውያኑ 2016 ክሳቸውን አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱም ከአምስት ዓመታት በኋላ ሉዓላዊ ያለመከሰስ መብትን በመጥቀስም ነበር ውድቅ ያደረገው።

የሴኡል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህንን ውሳኔ በመሻርም ብያኔውን አስተላልፏል።

ደቡብ ኮሪያ በጃፓን መንግሥት ላይ ስልጣን አላት ያለው ፍርድ ቤቱ ለዚህም ሴቶቹ በጃፓን ውስጥ ይኖሩ ስለነበር እና ህጋዊ ያልሆነ ተግባርም ስለተፈጸመባቸው እንደሆነም ጠቅሷል።

“ሉዓላዊም ይሁን ምን ህገወጥ ድርጊቶች ሲፈጸመው የትኛውንም የመንግሥትን ያለመከሰስ መብት የማይቀበል የጋራ አለም አቀፍ እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል” ብሏል።

ሊ ዮንግ ሱ የተባሉ የ95 ዓመት ተሟጋች እና ሰለባ ፍርድ ቤቱ ላስተላለፈው ብይን በሚያመሰግኑበት ወቅት በስሜት ተሞልተው ነበር።

ከፍርድ ቤት ሲወጡም “አመሰግናለሁ፣ በጣም አመሰግናለሁ” ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ብያኔውን ሳያዩ በሞት ለተለዩት ተጎጂዎችም ውሳኔውን መንገር ቢችሉም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለጃፓን ወታደሮች ሲባል ከ200 ሺህ በላይ ሴቶች እና ታዳጊዎች ለአስገዳጅ ወሲባዊ ንግድ ተዳርገዋል ተብሎ ይገመታል።

በነዚህ የወታደራዊ የወሲብ ንግድ ቤቶች ውስጥ ከነበሩት መካከል አብዛኛዎቹ ኮሪያውያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከቻይና፣ ፊሊፒንስ፥ ኢንዶኔዥያ እና ታይዋን የመጡ ነበሩ።

የጃፓኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮኮ ካሚካዋ ውሳኔውን “የሚያሳዝን እና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው” እንደሆነ ተናግረዋል።

“ የኮሪያ ሪፐብሊክ የተጣሰውን የዓለም አቀፍ ህግ እንዲያስተካከል ተገቢውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወስድ ጃፓን በድጋሚ አጥብቃ ትጠይቃለች” ሲሉም ተናግረዋል።