አል ሺፋ ሆስፒታል

ከ 5 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚገኘው የአል ሺፋ ሆስፒታል ላይ ከከፈተው አወዛጋቢ ዘመቻ አንድ ሳምንት በኋላ ለጥያቄ በሚል የሆስፒታሉን ዳይሬክተር አስሯል።

ዶክተር ሞሃመድ አቡ ሳልመያ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ህመምተኞችን ወደ ደቡባዊ የጋዛ ክፍል አጅበው በመውጣት እንደነበሩ ባልደረባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ሆስፒታሉ “የሐማስ የዕዝና ቁጥጥር ማዕከል ሆኖ እንዳገለገለ ማስረጃ ከመኖሩ ጋር” በተያያዘ ለጥያቄ መታሰራቸውን ገልጿል። ሆኖም ኃላፊውም ሆነ ሃማስ ይህንን ክስ አይቀበሉትም።

በሌላ ዜና በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ ሌላ ሆስፒታል አካቢ ከባድ ተኩስ እንደሚሰማ ተዘግቧል።

የኢንዶኔዥያው ቤት ላኻያ በተሰኘው ሆስፒታል የሚሰሩ አንድ ዶክተር የእስራኤል ወታደሮች ሁሉም ሰዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል። የእስራኤል ጦር ሁኔታውን እያጣራሁ ነው ብሏል።

ከሳምንታት በፊት ሀማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት በሚል ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በጋዛ ሰርጥ ላይ ከፍታለች። እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት የጋዛ ሰርጥ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች። በተቀናጁ ጥቃቶችም እስካሁን ሺህ 500 ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም አብዛዎቹ ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋዛ ሰርጥ ወደ ህጻናት መቃብር ስፍራም እየተቀየረ መሆኑንም አሳስቧል።

ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛ ጦርነትም እስራኤልና ሐማስ 50 ህጻናትና ሴት ታጋቾችን በአራት ቀን የውጊያ ፋታ ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።

እስራኤል እና ሐማስን ስታደራድር የቆየችው ኳታር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ለቀናት የሚቆየው ጦርነት የማቆም ፋታ ነገ አርብ በጋዛ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 1 ሰዓት እንደሚጀምር አስታውቃለች።

ሐማስ ደግሞ በስምምነቱ መሠረት የመጀመሪያዎቹን 13 ታጋቾች አርብ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ ይለቃል ተብሏል።

በሐማስ ታግተው ከነበሩት መካከል ቀድመው የሚለቀቁት ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚሆኑ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መጂድ አል-አንሳሪ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ታጋቾቹን ነገ ከሰዓት ከሐማስ የሚረከበው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

በጋዛ ትልቁ በሆነው አል ሺፋ ሆስፒታል ወደ 250 የሚገመቱ ህመምተኞችና ሰራተኞች እንደሚቆዩ ተገልጿል። ሆኖም ሆስፒታሉ የቀድሞ አገልግሎቱን መስጠት አይቀጥልም።

ባለፈው ረቡዕ 190 ታማሚዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ አስታማሚዎቻቸውና በርካታ የህክምና ባለሙያዎች እጀባ በተደረገለት አምቡላንስ በዓለም ጤና ድርጀት አማካኝነት ከሆስፒታሉ ወጥተው ወደ ደቡባዊ ጋዛ መዘዋወራቸውን የመንግስታቱ ድርጀት ገልጿል።