ሚላድ ዞህሬቫንድ

ከ 5 ሰአት በፊት

ኢራን ባለፈው ዓመት ከተቀሰቀሰው ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ሞት የተፈረደበትን ግለሰብ በድብቅ ገድላዋለች ሲሉ ምንጮች ለቢቢሲ ፐርዢያ ተናገሩ።

የ21 ዓመቱ ሚላድ ዞህሬቫንድ በሃማዳን ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ሐሙስ ጠዋት ተገድሏል ተብሏል።

ሄንጋው የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ግድያውን በተመለከተ ሪፖርቶች እንደደረሱት ገልጿል።

በተቃውሞ ሰልፉ ወቅት ዞህሬቫንድ የአብዮታዊ ዘብ አባልን በመግደል ጥፋተኛ ያለው የኢራን የፍትህ አካል ምንም ማረጋገጫ አልሰጠም።

ምንጮቹ አክለውም ግለሰቡ በእስሩም እና ፍርድ ቤት በተመላለሰባቸው ጊዜያት ሁሉ ጠበቃ ተከልክሏል ብለዋል።

ግድያው ከተረጋገጠ ዞህሬቫንድ ካለፈው ዓመት የተቃውሞ ሰልፎች ጋር ተያይዞ የተገደለው ስምንተኛ ሰው ይሆናል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ እንዳስጠነቀቁት ቀደም ባሉት ሰባት ጉዳዮች “የፍትህ አሰጣጡ ተገቢውን ሂደት እና ፍትሃዊ የዳኝነት መስፈርቶችን እንዳላሟላ” መረጃዎች ያመለክታል ብለዋል።

አክለውም “በቂ እና ወቅታዊ የሕግ ውክልና ማግኘት በተደጋጋሚ ተከልክለዋል። በደረሰባቸው ማሰቃየት ምክንያት በግዳጅ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

መህሳ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ሴት ሂጃቧን “ያለአግባብ” ለብሳለች ተብላ በሥነ ምግባር ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ መሞቷን ተከትሎ ነው እአአ መስከረም 2022 የኢራን መንግሥት ከባድ የተቃውሞ ሰልፍ ያጋጠመው።

የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገድሉ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል።

ሚላድ ዞህሬቫንድ ሐሙስ ረፋድ ላይ በሃማዳን ማዕከላዊ እስር ቤት እንደተገደለ ሁለት የመረጃ ምንጮች ለቢቢሲ ፐርሺያ ተናግረዋል።

የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት አስከሬኑን ከሰዓት በኋላ ለቤተሰቦቹ አላስረከቡም ሲሉ አክለዋል።

በኢራን የኩርድ ጎሣዎች ላይ የሚያተኩረው ሄንጋው በመግለጫው እንዳስታወቀው ዞህሬቫንድ ግድያው የተፈጸመበት መቼ እንደሆነ ያልተገለጸለት ከመሆኑም በላይ ለመጨረሻ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር እንዲገናኝም አልተፈቀደለትም።

“በሕይወት የመኖር መብትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን የታራሚውን እና የቤተሰቡን ሰብዓዊ መብት የሚጋፋ ነው” ያለውን ግድያም በጽኑ አውግዟል።

ሄንጋው አክሎም በኢራን ውስጥ ዋነኛው ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃይል ሆነው የአብዮታዊው ዘብ ግድያውን እንዲፈጽሙ በባለሥልጣናት ላይ ጫና አድርጓል ሲል ከሷል።

ውሳኔው የተፈጸመው ዞህሬቫንድ ገደሎታል ከተባለው መኮንን ቤተሰብ ግልጽ ፍቃድ ሳይኖር ነው ብሏል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአብዮታዊ ዘብ አባል በሆነው በአሊ ናዛሪ ግድያ የተከሰሰው ግለሰብ ላይ የሞት ፍርድ ማስተላለፉን የሃማዳን ዐቃቤ ሕግ ባለፈው ሳምንት አረጋግጧል ብሏል።

የተከሳሹን ማንነት ባይገለጽም የሕግ ባለሙያዎች ኅብረት የሆነው ደድባን ምንጮቹን ጠቅሶ ተከሳሹ ዞህሬቫንድ መሆኑን አስታውቋል። ቤተሰቦቹ ገዳዩን ይፋ እንዳያደርጉት ጫና እንደተደረገባቸውም አክሏል።

ናዛሪ ጥቅምት 2022 ለተቃውሞ ከወጡ የማሌየር የሕክምና ሳይንስ ፋኩልቲ ተማሪዎች ጋር ንትርክ ውስጥ ሲገባ ጭምብል ለብሰው ጥይት ከተኮሱበት አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ዞህሬቫንድ ነው በሚል በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶበታል።

በየዓመቱ በሚፈጸም የሞት ፍርድ ኢራን ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ኢራን በርካታ የሞት ቅጣት እየፈፀመች ነው ብሏል።

በ2023 የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ቢያንስ 419 ሰዎችን ተገድለዋል። ይህም ከ2022 ከተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ30 በመቶ ጭማሪ አለው።