
November 24, 2023 – Addis Admas
Written by Administrator

• ማህበሩ 70 ቢሊዮን ብር ለብድር ማቅረቡ ተነግሯል
የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር የተመሰረተበትን የ25ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በመጪው ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር ተገለፀ፡፡
በዝግጅቱ ላይ በአገሪቱ በልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውና የ25 ዓመታት እድሜ ያስቆጠረው የማይክሮፋይናንስ ዘርፍ ኅዳር 18ን “የኢትዮጵያ የብድርና ቁጠባ ቀን” በማለት እንደሚሰይም ተነግሯል፡፡
በማህበሩ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች እንደሚሳተፉ የጠቆመው የማህበሩ መግለጫ፤ ክብረ በዓሉ በፓናል ውይይትና ኤግዚቢሽን እንዲሁም ጥናቶች በሚቀርቡበት ኮንፍረንስና ሌሎች ኹነቶች እንደሚከበር አመልክቷል፡፡
ክብረ በዓሉ በመጪው ሳምንት ከህዳር 18-21 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ለአራት ተከታታይ ቀናት፣ በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ይከበራል፡፡
የ25ኛ ዓመት በዓል አከባበሩን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ ዳሙ ሆቴል አጠገብ ወደ ፒኮክ መናፈሻ መግቢያ ላይ በሚገኘው የማህበሩ አዳራሽ ፣ የማህበሩ የቦርድና የማኔጅመንት ከፍተኛ አመራሮች ለሚዲያ ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዓሉ “ማይክሮፋይናንስ በዲጂታል ዘመን፣ የፋይናንስ አካታችነት ለስራ ፈጠራና ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑን ያመለከተው ማህበሩ፤ ባለፉት ዓመታት በዋናነት የዲጂታል ስርዓት በማስፋፋትና በፋይናንስ አካታችነት ረገድ ጉልህ ስኬት መቀዳጀቱን ጠቁሟል፡፡
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የዲጂታል ሥርዓት ተጠቃሚ መሆናቸው በተጨባጭ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በቴክኖሎጂው አማካኝነት የተደራሽነት ሽፋናቸውን ቀድሞ ከነበረው 35 በመቶ ገደማ ወደ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ማሳደጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ከ50 የማህበሩ አባላት መካከል በ30 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የኮር ባንኪንግ ዲጂታል ሥርዓት መተግበሩን የገለጹት አመራሮቹ፤ በፋይናንስ አካታችነት ረገድም ከባንኮች ይልቅ ተቋማቱ የበለጠ ስኬት መቀዳጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ስድስት የሚሆኑ የማህበሩ አባላት ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን መስፈርት በማሟላት ወደ ባንክ ማደጋቸውንና በሂደት ላይ የሚገኙም እንዳሉ የጠቆሙት አመራሮቹ፤ ተቋማቱ ወደ ባንክ ሽግግር ቢያደርጉም የቀድሞ አገልግሎታቸውን የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ማህበሩ የሴቶች ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድም ትርጉም ያለው ሥራ ማከናወኑን የተናገሩት አመራሮቹ፤ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለሴቶች ሲቀርብ የነበረው ብድር አነስተኛ ቢሆንም፣ በሂደት እየተሻሻለ መጥቶ በአሁኑ ወቅት የብድሩ መጠን 50-50 (እኩል ለእኩል) ለመሆን መብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡ ለሴቶች ተስማሚ የሆነ የብድር አገልግሎት ለመተግበር ጥረት መደረጉንና የሴቶች ተሳትፎም ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱን አክለው ገልፀዋል፡፡
በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚቆጥቡ ደንበኞች ከ20 ሚ. በላይ እንደሚደርሱ የተነገረ ሲሆን፤ ማህበሩ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ለብድር ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር ባለፉት 25 ዓመታት ስኬት ብቻ አይደለም የተቀዳጀው፤ ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች እንዳገጠመውም የማህበሩ አመራሮች በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
ከተግዳሮቶቹም መካከል የፋይናንስ እጥረት በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡ የተጀመረውን ኮር ባንኪንግ ተግባራዊ ለማድረግ ማህበሩ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ገጥሞት ነበር ያሉት አመራሮቹ፤ የውጭ ምንዛሬ በፈለግነው ጊዜና መጠን ባለማግኘታችንም ተቸግረን ነበር ብለዋል፡፡ ሆኖም ማህበሩ ችግሩን ከተቋማቱ ጋር በጥምረት በመስራት ለመፍታት እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡
የመሰረተ ልማት ችግር ሌላው የገጠማቸው ተግዳሮት እንደነበር የጠቆሙት የማህበሩ አመራሮች፤ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ሥራቸውን እያስተጓጎለባቸው ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመው፣ ከፍተኛ አቅም ያለው ጄነሬተር በመጠቀም አገልግሎታቸውን ያለማቋረጥ ማቅረብ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
ከሁሉም በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ትልቅ ተግዳሮት የሚያበድሩት ካፒታል ማነስ መሆኑን በይፋ የገለፁት የማህበሩ አመራሮች፤ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃን ስለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና አገልግሎታቸው ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ በመስጠትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ እግረ መንገዳቸውን በመግለጫው ላይ ለተገኙት የመገናኛ ብዙሃን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
