November 24, 2023 

በወልደያ የተፈፀመው የ25 ደቂቃ ልዩ ኦፕሬሽን!

የአማራ ደም መላሽ፤ የጠላት ረመጥ እየተባለች ትጠራለች፤ ጠላት በክፉ ዓይን የሚመለከታት ከተማ ናት፡፡

በወያኔ ወረራ ወቅትም ጠላት የጭካኔ በትሩን ያሳረፈባት ስትሆን፤ እሷን ለቆ ሲወጣ የሽንፈቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ ይህች ከተማ የሰሜን ወሎ መናገሻዋ ወልድያ ናት፡፡ ወልድያ ዛሬ ሌሊት በነበልባል ልጆቿ ብርታት በግፍ የታጎሩባትን ልጆቿን ከግፈኛው እስር ቤት አስወጥታለች፡፡ ከሌሊቱ 6፡00 ላይ የተፈጸመውን ኦፕሬሽን አስመልክቶ፤ የኢትዮ 251 ምንጮቻችን፤ ‹‹የፋኖ አስደናቂ ጉዞ ብቻ ሳይሆን ከመብረቅ የፈጠነ ኦፕሬሽን በወልድያ ተፈጽሟል›› ሲሉ መረጃውን መናገር ይጀምራሉ፡፡

ምንጮቻችን ስለኦፕሬሽኑ ሲገልጹ፤ ‹‹ለወራት የታቀደዉ ግዳጅ ዛሬ በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡ ወልድያ ማረሚያ ቤት ዉስጥ ስልጠና እና አደረጃጀት ተፈጥሮ ፋኖን ሲጠባበቅ የነበረው አንድ ብርጌድ የፋኖ ጦር፤ ዛሬ ምሽት ከማረሚያ ቤቱ በፈጣን ተዋጊው ፋኖ ነጻ መውጣቱን ከምሥራቅ አማራ ፋኖ መረጃ ክፍል አረጋግጠናል። ታላቁ ተዋጊ አሸናፊ (ቆጥረህ ጫን)እና ብዛት ያላቸው የአማራ ልጆች ለዓመታት በግፍ እያማቀቀ የሚገኘው ወልድያ ማረሚያ ቤት ዛሬ ሌሊት 6፡00 በተደረገ ትግል በምሥራቅ አማራ ፋኖ ቁጥጥር ስር ገብቷል›› ብለዋል፡፡

በተካሄደው ልዩ ኦፕሬሽንም፤ 687 ንጹሃን አማራዎች ከእስር ተለቀዋል፡፡ አገዛዙ ካደረበት የአማራ ጥላቻ በተቀዳ ጭካኔው፤ በፖለቲካ ልዩነት እና ፋኖ ናችሁ ፋኖንም ትደግፋላችሁ ተብለው የታሰሩ የሰሜን ወሎ ወጣቶችን በግፍ ሲያሰቃይበት የነበረውን እስር ቤት ፋኖ በወሰደው መብረቃዊ ኦፕሬሽን ማስለቀቅ ችሏል፡፡ ኦፕሬሽኑን የመራው የምሥራቅ አማራ ፋኖ አሳምነው ብርጌድ ዋና አዛዥ ፋኖ በለጠ ሸጋው በሰጠው አስተያየት፤ ‹‹25 ደቂቃ ልዩ ኦፕሬሽን ነው ያደረግነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ ፋኖ በለጠ አክሎም፤ ‹‹ኦፕሬሽኑን ያደረግነው በከፍተኛ ጥናትና ዝግጅት ነው፡፡ ባደረግነው አጭር ኦፕሬሽን አገዛዙ በግፍ ያሰራቸውን ከ680 በላይ የአማራ ልጆችን ከእስር ቤቱ አስወጥተናል›› ብሏል፡፡

ፋኖ በለጠ ሸጋው ከዚህ ቀደምም በአገዛዙ ወራሪና ጨፍጫፊ ሠራዊት ላይ ተደጋጋሚ ኦፕሬሽኖችን አካሂዶ ኪሳራ ያደረሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ፋኖ በለጠ ሸጋው በአንድ የገጠር ቀበሌ ህዝብን በሚወይይበት ወቅት፤ ‹‹የአማራ ህዝብ ይህን እጣ ፋንታው ይህን አገዛዝ ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻልን እመኑኝ አንዳችንም በህይወት እንድንኖር አይፈቅዱልንም፡፡ እኛ የምንዋጋው በህይወት እንዳንኖር ሊያጠፋን የመጣ ጠላት ስለገጠመን እንጂ፤ በግላችን የደረሰብን መገፋ ስላለ አይደለም፡፡ እኔ በግ የኮራ ደመወዝ የሚከፈለኝ እንደነበረ ሁሉም ያውቃል፡፡ ነገር ግን እንኳን ደመወዜን እኔንም ማትረፍ የምችለው ሊያጠፋን የመጣውን ጠላት ከወገኔ ጋር ሆኜ ተዋግቼ ሳሸንፍ ብቻ ነው›› ሲል መናገሩን በኢትዮ 251 ሚዲያ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡

Mulugeta Anberber