
25 ህዳር 2023, 11:08 EAT
በኔትፍሊክስ አማካይነት እየታየ የሚገኘው ስኩይድ ጌም፡ ዘ ቻሌንጅ የተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተሳታፊዎች በቀረጻ ወቅት ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ሊጠይቁ መሆኑን ጠበቃቸው ገለጹ።
ሁለት ደንበኞችን የወከሉት ጠበቃ ከደንበኞቻቸው መካከል አንዱ ረዘም ላለ ሰዓት ለከፍተኛ ቅዝቃዜ በመጋለጡ የጤና መቃወስ እንዳጋጠመው፣ ሌላኛው ደግሞ የነርቭ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
በኔትፍሊክስ የቀረበው ይህ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ብዙ ተወዳጅነትን ባተረፈው የደቡብ ኮሪያው ስኩይድ ጌም ድራማ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎች 4.56 ሚሊዮን ዶላር ለማሸነፍ ሲጫወቱ ይታያል።
የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ አዘጋጆች ቃል አቀባይ ለተሳታፊዎቻችንን ደኅንነት ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን ብለዋል።
ጠበቆች እንደሚሉት በስም ያልጠቀሷቸው ተሳታፊዎች ጉዳት የደረሰባቸው “በቀረጻ ወቅት በቀዝቃዛ ቦታ ላይ ሳይንቀሳቀሱ ለረዥም ሰዓት መቆየት ስለነበረባቸው ነው” ብለዋል።
- ሐማስ 24 ታጋቾችን ሲለቅ አስራኤል 39 እስረኞችን ፈታች20 ህዳር 2023
- እስራኤል የምትለቃቸው ፍልስጤማውያን እስረኞች እነማን ናቸው? ለምንስ ታስረው ቆዩ?25 ህዳር 2023
- በታጠቁ እስረኞች የሚጠበቀው እና ውጪውን ዓለም የሚያስንቀው ቅንጡው እስር ቤት25 ህዳር 2023
የሕግ ባለሙያው ዳንኤል ስሌድ “ተሳታፊዎች ለውድድር ሲመጡ ቀላል እና አዝናኝ በሆኑ ውድድሮች ተሳታፊ የሚሆኑ መስሏቸው” ነበር ብለዋል።
“ለረዥም ሰዓት ለከፍተኛ ቅዝቃዜ ተጋልጠዋል። . . . ከተሳታፊዎች መካከል አንዱ በቅዝቃዜው ምክንያት የእጁ ቆዳ ቀለም ተቀይሯል” ብለዋል።
የሕግ ባለሙያዎቹ በሥራ ቦታ የነበረው የጤና እና የደኅንነት ጥበቃ ደረጃ ደካማ መሆኑን በመጥቀስ በደንበኞቻቸው ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ዝርዝረው የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ለሚያዘጋጀው ስቱዲዮ ላምበርት ልከናል ብለዋል።
በዚህ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ አንዱ ጨዋታ ከተጫዋቾች ፊት ርቆ የተሰቀለች አሻንጉሊት ጀርባዋን ለተጫዋቾች ሰጥታ ስትዘምር ተጫዋቾች በፍጥነት ወደፊት ተራምደው ውድድር መጨረስ ይጠይበቅባቸዋል። ታዲያ አሻንጉሊቷ ፊቷን ወደ ተጫዋቾች ስታዞር ሁሉም ተሳታፊዎች ባሉበት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ መቆም ይኖርባቸዋል።
ታዲይ ይህን ውድድር ለማጠናቀቅ ተሳታፊዎች እስከ አምስት ሰዓታት እንደፈጀባቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ገልጿል።
ኔትፍሊክስ ከዚህ ቀደም በቀረጻ ወቅት ሦስት ሰዎች መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟቸው የሕክምና ድጋፍ ማግኘታቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አሉ መባሉን ግን ሐሰት ነው ብሏል።
ስኩይድ ጌም፡ ዘ ቻሌንጅ የተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት በኔትፍሊክስ ላይ ብዙ ተመልካች ካላቸው በእውነት ላይ የተመሠረቱ ፕሮግራሞች አንዱ ነው።
