
25 ህዳር 2023, 10:36 EAT
በመላው ዓለም በተለይም በአሜሪካ ከባድ ተቃውሞን ያስከተለውን አፍሪካ አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው የቀድሞ የፖሊስ አባል እስር ቤት ውስጥ በጩቤ ተወጋ።
የሚያኒያፖሊስ ግዛት የፖሊሰ መኮንን የነበረው ዴሪክ ሾቪን በግድያው ምክንያት ታስሮ በሚገኝበት የአሪዞና እስር ቤት ውስጥ ጥቃት እንደተፈጸመበት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ምንጮች ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት የ47 ዓመቱ ሾቪን በሌላ አስረኛ በተፈጸመበት የስለት ጥቃት ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
ኒው ዮርክ ታይምስም ጉዳዩን የሚያውቁ ሁለት ሰዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው የቀድሞው የፖሊስ መኮንን እስር ቤት ውስጥ ጥቃት እንደተፈጸመበት አረጋግጧል።
ዴሪክ ሾቪን ፖሊስ በሚፈጽመው የጭካኔ ድርጊት እና ዘረኝነትን በመቃወም በመላው አሜሪካ ለተቀሰቀሱት መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች ምክንያት ከሆነው የጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎየድ ሞት ጋር በተያያዘ የረጅም ዓመታት እስር ተፈርዶበታል።
- የጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች31 ግንቦት 2020
- ዓለምን ያናወጠውን ቪዲዮ የቀረጸችው ታዳጊ፡ ሰው ሲገደል መቅረጽ፤ ጽድቅ ነው ኩነኔ?15 ሰኔ 2020
- ዴሪክ ሾቪን በጆርጅ ፍሎይድ የግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ21 ሚያዚያ 2021

የአሜሪካ የእስር ቤቶች አስተዳደር ቢሮ ባወጣው መግለጫ በቱክሰን ከተማ ውስጥ በሚገኝ የፌደራል መንግሥቱ እስር ቤት ውስጥ አንድ እስረኛ አርብ ምሽት በስለት መወጋቱን አረጋግጧል።
ቢሮው ጨምሮም የአስር ቤቱ ሠራተኞች ከሰተቱን በመቆጣጠር ጉዳት የደረሰበትን እስረኛ ሕይወት ለመታደግ “የነፍስ አድን ተግባራትን” በመፈጸም ወደ ሆስፒታል መወሰዱን አመልክቷል።
ነገር ግን መግለጫው ጉዳት የደረሰበት አስረኛን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ዴሪክ ሾቪን ከጥቃቱ በሕይወት የተረፈ ሲሆን፣ ከእሱ ውጪ ሌላ ጉዳት የደረሰበት ሰው እንደሌለም ተገልጿል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ዴሪክ ሾቪን ከጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ፍትሃዊ በመሆነ መንገድ አልታየልኝም በሚል ያቀረበውን ቅሬታ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ካደረገበት ከቀናት በኋላ ነው።
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ከሦስት ዓመት በፊት ለሕልፈት የበቃው ነጩ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪን መሬት ላይ አስተኝቶ አንገቱ ላይ በጉልበቱ በመርገጥ ከዘጠኝ ደቂቃዎች በላይ ከያዘው በኋላ ነበር።
ይህንን ክስተት በአካባቢው የነበረች አንዲት ወጣት በስልኳ ካሜራ ቀርጻ ካሰራጨችው በኋላ ፖሊሶች በሚፈጽሙት ዘር ተኮር በደል ላይ ከአሜሪካ ባሻገር በመላው ዓለም ቁጣ እና ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በዚህ ድርጊት ለእስር የተዳረገው ሾቪን ከፍሎይድ ግድያ ጋር በተያያዘ በቀረቡበት ክሶች የ22 ዓመት አስር የተፈረደበት ሲሆን፣ በማስከተል ደግሞ የሟቹን መብት በመጣስ ተጨማሪ የ20 ዓመት እስር ተበይኖበታል።
