ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን ታጣቂዎች 11 የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል ሠራተኞችን ከአንድ ወር በፊት በኃይል እንዳገቱ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።
ታጣቂዎቹ የማዕከሉን ሠራተኞች ያገቷቸው፣ ለማዕከሉ ሥራ ከቢሾፍቱ ወደ ባቱ ከተማ ከተማ በተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል። የቡድኑ ታጣቂዎች ሠራተኞቹን በትክክል የት ቦታ ላይ አፍነው እንደወሰዷቸው ግን ማወቅ አለመቻላቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ፣ አስራ አንዱን ሠራተኞች ለመልቀቅ በድምሩ አምስት ሚሊዮን ብር እንደጠየቁ የጠቆሙት ምንጮች፣ የታጋቾች ቤተሰቦችም ገንዘቡን አዋጥተው እንደከፈሉ ተናግረዋል።
ኾኖም አጋቾቹ ሌላ ተጨማሪ ኹለት ሚሊዮን ብር በመጠየቃቸው፣ ታጋቾቹ እስካኹን እንዳልተለቀቁ ዋዜማ አረጋግጣለች።
