November 25, 2023 

በአማራ ክልል አዊ ብሄረሰብ ዞን የሚገኘው ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ሥራ ማቆሙን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

በፋብሪካው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ጣቢያ ላይ ከዓመት በፊት በተፈጸመ የመለዋወጫ ዕቃዎች ሥርቆት የተነሳ፣ ፋብሪካው እስካኹን የኤሌክትሪክ ኃይል ሳያገኝ መቆየቱን ዋዜማ ተረድታለች።

ፋብሪካው እስካለፈው ዓመት ግንቦት ድረስ በነዳጅ አማካኝነት ሲያመርት ቢቆይም፣ ክረምቱን በኃይል ጣቢያው ላይ ጥገና ተደርጎለት እንደገና ሥራ ይጀምራል ተብሎ ተጠብቆ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ኾኖም የኃይል አቅርቦት ችግሩ ለጊዜው ባለመስተካከሉ፣ በቀጣዩ ጥር ሥራ ይጀምራል እንደተባለ ምንጮች ገልጸዋል።

የሸንኮራ አገዳ አቅራቢ ጋሪዎች እጥረት ማጋጠሙም፣ ለፋብሪካው ሥራ ማቆም ተጨማሪ ምክንያት እንደኾነ ተነግሯል።

ፋብሪካው፣ ከ1 ሺህ 500 መቶ በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉት። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።