November 25, 2023 

ህዳር 14/1967 ዓም፡ ባልታወጀው ቀይ ሽብር ያለቁት

የቀድሞው መንግስት ባለስልጣናት የተረሸኑበት ቀን  =  መንግስቱ ሙሴ

==================================

1967 ዓም የደርግ ወታደራዊ መንግስት 60 የሚሆኑ የቀድሞው መንግስት ባለስልጣኖችንና ወታደራዊ መኰንኖች ያለፍርድ ልክ በዛሬው ቀን በግፍ ገድሎ በቀድሞው የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ ውስጥ በጅምላ ቀበራቸው፡፡ ይህ የጅምላ መቃብር በኢትዮጵያ የጀመረው በዚህች በሕዳር 14/1967 ዓም ሲሆን እስከዛሬ የቀጠለው የጅምላ ጭፍጨፋ እና የጅምላ መቃብር በሐገራችን በደርጉ መንግስቱ ኃይለማርያም እና ግብረአበሮቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በአርበኝነት ታላላቅ ጀብዱ የሰሩ፤ ሐገራቸውን በአለም መድረክ ክብር እና ሞገስ እንድትይዝ ያደረጉ ከጠቅላይ ሚኒስቴር አክሉሉ ሐብተወልድ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ትውልድ የአርበኛው ልጅ እና አክሊሉን ወክለው ለአጭር ግዜ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቦታውን ይዘው የነበሩት የቢትወደድ መኮነን እንዳልካቸው ልጅ እንዳልካቸው መኮነንን፤ የአርበኛው የበኛው እና መስዋእትነትን በደቡብ ኢትዮጵያ ጠላትን ሲከላከሉ የወደቁት የልዑል ራስ ደስታ ዳምጠው እና የልእልት ተናኘወር ልጅ፤ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኮማንደር የነበረው አድሚራል እስክንድር ደስታን ጨምሮ በእብነበለ ፍርድ የተገደሉበት ክፉ ቀን ነበር።

ነገሩ እንዲህ ነው: — ህዳር 14 ቀን 1967 ደርግ ጽ/ቤት በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወይም መንግሥት በጠቅላላ ጉባኤ እና በቋሚ ኮሚቴነት ንዑሳን ኮሚቴነት የተዋቀሩትና ሥልጣን በብቸኝነት ይዘው ያሉት ቡድኖች «ለፖለቲካ እስረኞች የፖለቲካ ውሣኔ ለመስጠት» በዚህ ቀን በደርግ ጽ/ቤት ጠቅላላ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ሰው መግደልን አጀንዳ አድርገው ተወያይተው ለመግደልም ተስማምተው በእነርሱ ቁጥጥር ስር የነበሩ ሰዎችን «ፊውዳል፣ መኳንንትና መሣፍንት ስለሆኑ ደማቸውን የንፁህ ሰው ደም እንደፈሰሰ አንቆጥረውም፤ ጨቋኞች ናቸው።» በማለት እንዲገደሉ በአንድነት ወስነው በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ውስጥ 59 ሰዎች በጥይው ተደብድበው አንዲገደሉ አደረጉ፡፡ በዚህ የግፍ ጭፍጨፋ ሊተባበሩ ያልፈለጉት ክቡር ጄኔራል አማን አንዶም በታንክ ተከበው እጃቸውን ባለመስጠት ተሰውተዋል።

እነዚህ ታላላቅ ሰወች ምንም እንኳን በያሉበት ታድነተው እንዲያዙ ሐምሌ 11 ቀን 1966 በሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም የተፈረመ ተዕዛዝ ቢሰጥባቸውም ሃምሳ አምስቱ የንጉሱ ከፍተኛ ሚኒስትሮች፤ ጄኔራሎች፤ እና ከፍተኛ ሃላፊዎች በፈቃዳቸው እጃቸውን የሰጡ ነበሩ፡፡ ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የቀድሞ ንጉሥ ቀዳማዊ የኃይለስላሴን ባለሥልጣናት ሰብስቦ አራተኛ ክፍለ ጦር ከአጎረ በኋላ ጥቅምት 11 ቀን 1967 በሰጠው የንቅናቄ ትዕዛዝ ወደታላቁ ቤተመንግሥት አንዲዛወሩ አደረገ፡፡

«ከኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ ስተዳደር ደርግ ህዳር 6 ቀን 1967 በቁጥር አ/ ደ/ቸ/6/2325 የተጻፈልንን ደብዳቤ እናስታውሳለን፡፡ በ1966 የመርማሪ ኮሚሽን አዋጅ አንቀጽ10 እንደተመለከተው ኮሚሽኑ ስለወሎ ድርቅ፣ረሃብና እልቂት ባደረገው ምርመራ መሠረት ከዚህ ጋር በተያያዘው አባሪ ላይ በተመለከቱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ተለይቶ የተመለከተው የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው እናስታውቃለን፡፡

አባሪው ላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ሲባል በግፍ ያለፍርድ ከተገደለት ውስጥ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ፣ ጄኔራል ከበደ ገብሬ ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ አቶ ሙላቱ ደበበ ፣ ዶክተር ተስፋዬ ገብረእግዚ ይገኙበታል፡፡ አቶ ሰይፉ ማህተመ ስላሴና ደጃዝማች ካሣ ወልደማርያም በሌላ ዙር ከተገደሉት ውስጥ ናቸው፡፡ አነዚህ ያፍርድ የተገደሉ ባለሥልጣኖች በመርማሪ ኮሚሽን የምርመራ ውጤት መሠረት ይጠየቁበታል የተባለው ወንጀል በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥ 412 የሥራ ግዴታን ተግባር መጣስ እና ቁጥር 509 ችግር ወይም ረሃብ እንዲመጣ ማድረግ የሚል ነበር፡፡

በዚህ እብነበለ ፍርድ ስብሰባ ላይ የተገኙ የደርግ አባላት 93 ነበሩ፡፡ በድምጽ አሰጣጡ ዝርዝር ከፍተኛው ድምጽ በ93 መቆሙ ይታያል፡፡ የስብሰባው ቃለ ጉባኤ በወቅቱ የደርግ ዋና ፀሐፊ በነበረው በሟቹ በሻምበል ገብረየስ ወልደሃና መጻፉ በፖሊስ ላብራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል፡፡ ስብሰባው እንዴት እንደተጀመረ፣ እደተመራና እንደተፈፀመ፣ ከደርግ አባላት ውስጥ እነማን እንደተገኙ ምንና እዴት እንደወሰኑ በኋላ በወያኔ ዘመን የተጠሩ ምስክሮች ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡

በደርጉ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ 2ኛ መዝገብ የሠፈረው የአፈፃፀም ቅደም ተከተል በአይን ምስክሮችም ተደግፏል፡፡በውሳኔው መሰረትም አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ተገኝተው ሞት የተወሰነባቸው ሰዎች ቅጣቱን በትክክል ማየታቸውን እነዲያረጋግጡ ዘጠኝ የደርግ አባላት ሲመረጡ የደርጉ የእስረኛ አስተዳደር ፣ የመከላከያ፣ የደህነነትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እዲያስተባብሩ በደርጉ ጠቅላላ ጉባኤ ተወስኖ እርምጃው ተወሰደ ይላሉ፡፡ህዳር 14 ማታ ብረት ያልያዙ እስረኞች እና ለዘመናት ሀገራቸውን ከማይጮ እና ሽሬ ዘመቻወች እስከ የተባበሩት መንግስታት አዳራሽ ቆመው የተከራከሩ ግብር እና ሞገሷን ያለበሱ እስካሁንም መሰል የሌላቸው ታላላቅ ሰወች እንደ አክሉሉ ኃብተወልድ አይነቶች በደናቁርት እና ጉግ ማንጉግ የመንግስቱ ተከታዮች የተኩስ እሩምታ 59 ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ተገደሉ፡፡

ለደርጉ ሃላፊዎች አዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ ውስጥ በአካል ተገኝተው የአፄ ኃይለስላሴን ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ተኩሰው የገደሉ የደርግ አባላት ስም ዝርዝርና የተኮሱት ጥይት መጠን በሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ ሪፖርት ተደረገ። በዚሁ መሠረት :

ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ- 43 ጥይት

ሻምበል ተፈራ- 32 ጥይት

ሻምበል ኃይሌ መለስ (ጀኔራል)- 25 ጥይት

ባሻ ተፈራ ጅፋር- 60 ጥይት

፶/አለቃ በቀለ ደጉ- 32 ጥይት

ፒ/ኦ ሚካኤል- 25 ጥይት

፶/አ ዳምጤ- 16 ጥይት

ወታደር ደጀኔ አ/አገኘሁ – 40 ጥይት

ወታደር ገ/ጊ ብርሃኑ- 50 ጥይት

ሻለቃ ባሻ ለማ ኩምሳ- 7 ጥይት

ም/፲/አ ግርማ አየለ-3 ጥይት

ይህን ያህል ጥይት በመተኮስ እና ከሌሎች ወታደሮች ጭምር በታጋች አርበኞች እና ለሐገር አገልጋዮች ላይ የጥይት መአት በማርከፍከፍ በወህኒቤቱ ግቢ ውስጥ መግደላቸውን በሁአላ በወጣ መረጃ ተረጋግጧል። ምንም እንኳን ውሳኔው የጋራ ይምሰል እንጅ አንዳንድ ምሁኢራንም በዚህ ጉዳይ እንደገቡበት ይታወቃል። ሆኖም ይህን ግድያ በዋናነት አስፈጻሚ እና አቀነባባሪው አንድ ትውልድ የጨረሰው መንግስቱ ኃይለማርያም እንደነበር እርግጥ ነበር። ይህ ሰው ዛሬ በህይወት እንደሚኖር ይታወቃል።

ተከታታይ አንባገነኖች አገራችንን እና ሕዝባችንን ብሎም እንቁ የሐገር ከፍታን ያሳዩ መሪወችን በየግዜው በመግደል እስከዛሬ ፍትህ ባለማግኘት ቀጥለዋል። የዛሬወቹ እንደተኳቸው ጨካኞች ሁሉ የሽግግር ፍትህ እናስፈጽማለን ብለው ያሾፋሉ። ይህ ቀልድ በወያኔ 1991 በደርግ 1967 ተሰብኳል። ዛሬ ኦነጋውያኑ “የምክክር ሸንጎ” ብለው በሰየሙት የሙታን ምሁራን ስብስብ ፍትህን እና እርቅን እናመጣለን ይበሉ እንጅ ከትውልድ አለፈው ዘር የማጥፋት ወንጀላቸው በሚሊዮኖች ቀጥለውበታል። ( ፀሐፊው መንግስቱ ሙሴ ነው )