November 26, 2023 – Addis Admas

Saturday, 25 November 2023 19:39
Written by Administrator
በቅርቡ አፍሮ ባሮሜትር በተባለው ታዋቂ የምርምር ተቋም ይፋ የተደረገውን የሕገ- መንግስቱ ማሻሻያ አስፈላጊነት፤ “ጊዜውን ያልጠበቀና ግልፅነት የጎደለው ነው” ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አጣጣሉት።
ተቋሙ የጥናቱ ውጤቱን ባለፈው ህዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሕገ መንግስቱ የፖለቲካና የሕግ ሰነድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ ከነባራዊው ሁኔታ አንፃር ጥናቱ በችኮላ መሰራት የነበረበት አይደለም ብለዋል።
አፍሮ ባሮሜትር የተሰኘው ይኸው የምርምር ተቋም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ጊዜ ገደብ ይጣልበት በሚለው ዙሪያና የሕገመንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል መደምደሚያ ያለው የጥናት ውጤት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።“ጥናቱ የሁሉንም ብሔሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ያላካተተ በመሆኑ በርከት ያሉ ጉድለቶች የተመለከትንበት የጥናት ሰነድ ነው” ሲሉ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አጣጥለውታል። አፈጉባኤ አገኘሁ እንደሚሉት ከሆነ፤ የጥናቱ ናሙናዎች ናቸው ተብለው የተወሰዱ መረጃዎች ግልፅነትና የውክልና ተአማኒነት የሚጎድላቸው ናቸው በማለት የጥናት ግኝቱን ተችተውታል።
ህገ-መንግስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች ቃልኪዳን ሰነድ እንደመሆኑ መጠን፣ ህዝቦች በህገ-መንግስቱ ዙርያ ካላቸው ልዩ ፍላጎት አንፃር የጥናት ውጤቱ “በመሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የሚጋጭ ነው” ብለዋል አፈጉባዔው።በአፍሮ ባሮሜትር ጥናት መሠረት፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን መገደብ አለበት የሚሉ ኢትዮጵያውያን 66 በመቶ ሲሆኑ፣ አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንድትሆን የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 53 በመቶ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ጥናቱ፤ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ 2400 ኢትዮጵያውያንን ቃለመጠይቅ በማድረግ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አፍሮ ባሮ ሜትር የተሰኘው ተቋም ያቀረበው የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፤ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ- መንግስት “መሻሻል አለበት” ብለዋል።
“ጥናቱ አካታችነት የጎደለው ነው። አፈጉባኤ አገኘሁ በበኩላቸው ጥቂት ልሒቃን አነጋግሮ እንዲህ አይነት ሰነድ ማቅረብ የህገ-መንግስቱን መሠረት በውል ካለመረዳት የሚመነጭ ነው” ሲሉ ተችተዋል።