
ከ 2 ሰአት በፊት
አንድ ታይላንዳዊ የቀድሞ ወታደር በሠርጉ ዕለት ሙሽራዋን እና ሌሎች ሦስት ሰዎችን ገድሎ ራሱን እንዳጠፋ የአገሪቱ ፖሊስ ለቢቢሲ አስታወቀ።
የ29 ዓመቱ ሙሽራ ቻቱሮንግ ሱክሱክ እና የ44 ዓመቷ ሙሽራ ካንቻና ፓቹንቱክ ጋብቻቸውን ባለፈው ቅዳሜ በሰሜናዊ ምሥራቅ ታይላንድ ውስጥ ነበር የፈጸሙት።
ሙሽራው የሠርጉ ድግስ እየተካሄደ ሳለ በድንገት ተነስቶ በመውጣት ሽጉጥ ይዞ ተመልሶ ነው ጥቃቱን የፈጸመው። በዚህም ሚስቱን፣ የ62 ዓመቷን የሙሽራዋን እናት እና እህቷን ከገደለ በኋላ እራሱን እንዳጠፋ ተዘግቧል።
በተጨማሪም ሙሽራው የተኮሳቸው ተባራሪ ጥይቶች ሁለት የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ታዳሚዎችን ያቆሰለ ሲሆን፣ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ የአንደኛው ግለሰብ ሕይወት አልፏል።
ፖሊስ ለቢቢሲ እንደገለጸው ሙሽራው “በወቅቱ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር” ነገር ግን ግድያውን ለመፈጸሙ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም ብሏል።
ጨምሮም ሙሽራው ሽጉጡን እና ጥይቶችን ባለፈው ዓመት በሕጋዊ መንገድ መግዛቱን አመልክቷል።
- በታጠቁ እስረኞች የሚጠበቀው እና ውጪውን ዓለም የሚያስንቀው ቅንጡው እስር ቤት25 ህዳር 2023
- በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ከ40 ዓመት በላይ የተፈረደበት ፖሊስ እስር ቤት ውስጥ በስለት ተወጋ25 ህዳር 2023
- ሩሲያ ፑቲንን በመተቸት የሚታወቁትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ‘የውጭ ወኪል’ ስትል ፈረጀች26 ህዳር 2023
የታይላንድ መገናኛ ብዙኃን ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ የሠርጉ ታዳሚዎችን ጠቅሰው እንደዘገቡት፣ ከጥቃቱ ቀደም ብሎ በሠርጉ ሥነ ሥርዓት ላይ በሙሽሮቹ መካከል ጭቅጭቅ ነበረ። እንዲሁም ሙሽራው በእሱ እና በሚስቱ መካከል ባለው የዕድሜ ልዩነት ምክንያት ጥሩ ስሜት ይሰማው እንዳልነበረም ተናግረዋል።
ነገር ግን ፖሊስ እየተባሉ ያሉት ነገሮች ሁሉ ከግምት የዘለሉ እንዳልሆኑ እና አስፈላጊውን ማስረጃ በመሰብሰባቸው ጉዳዩ “በቅርቡ” እንደሚዘጋ ገልጿል።
የታይላንድ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ሙሽራው እና ሙሽሪት ባለፈው ቅዳሜ ይፋዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ከማከናወናቸው በፊት ለሦስት ዓመታት አብረው ኖረዋል።
የቀድሞ የአገሪቱ ሠራዊት አባል የነበረው ሙሽራው በውትድርና አገልግሎቱ ወቅት በደረሰበት ጉዳት ቀኝ እግሩን ያጣ ሲሆን፣ በአካል ጉዳተኞች ስፖርት ውስጥ በመሳተፍ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመት በኢንዶኔዢያ በተካሄደው የእስያ የአካል ጉዳተኞች የስፖርት ውድድር ላይ በውሃ ዋና ተወዳድሮ የብር ሜዳሊያን ለማግኘት ችሏል። በሚቀጥለው ወር ታይላንድ በምታስተናግደው የዓለም የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ውድድር ላይ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን ይጠበቅ ነበር።
ታይላንድ ውስጥ የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆን የሚቻል ቢሆንም፣ የጅምላ ግድያ ግን ብዙም የተለመደ አይደለም።
ባለፈው ጥቅምት ወር በዋና ከተማዋ ባንኮክ በሚገኝ ቅንጡ የገበያ አዳራሽ ውስጥ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።
በተጨማሪም አንድ የቀድሞ ፖሊስ መኮንን በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ውስጥ በሚገኝ የሕጻናት መንከባከቢያ ውስጥ በጦር መሳሪያ እና በቢላ በፈጸመው ጥቃት 37 ሕጻናትን ገድሏል።
