ጥቃት የደረሰባቸው ተማሪዎች፣ ሁለቱ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙና አንደኛው ግን ለከፍ ጉዳት መዳረጉን ፖሊስ ገልጿል
የምስሉ መግለጫ,ጥቃት የደረሰባቸው ተማሪዎች፣ ሁለቱ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙና አንደኛው ግን ለከፋ ጉዳት መዳረጉን ፖሊስ ገልጿል

ከ 5 ሰአት በፊት

ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ቬርሞንት ግዛት ሦስት ፍልስጤማውያን ተማሪዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው ጉዳት ደረሰባቸው።

ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ጉዳዩን ጥላቻ መሠረት ያደረገ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ቤተሰቦቻቸው ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሂሳም አዋርታኒ፣ ታሃሲን አህመድ እና ኪናን አብዱልሃሚድ የተባሉት ተማሪዎች ከቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ከአንድ ግለሰብ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ በኋላ ተኩስ እንደከፈተባቸው ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን እየፈለገ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ላይ ለምን ጥቃተት እንደከፈተም ምርመራ እያደረገ ነው።

ተማሪዎቹ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ወቅት ኬፊያ የተባለውን እና በአረብ ባህል አንገት ወይም ጭንቅላት ላይ የሚደረገውን ዥንጉርጉር የአንገት ልብስ ለብሰው ነበር።

ከጥቃቱ በኋላ የሁለቱ ተማሪዎች ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የበርሊንግተን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ጆን ሙራ የገለጹ ሲሆን፣ አንደኛው ተማሪ ግን የከፋ ጉዳት እንደደረሰበት ጠቁመዋል።

ከሦስቱ ተማሪዎች መካከል ኪናን አብዱልሃሚድ በሃርቫርድ ኮሌጅ ውስጥ ተማሪ ሲሆን፣ የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ በብራውን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ከተጎጂዎቹ የአንዱ አጎት የሆነው ሪች ፕራይስ፣ ሦስቱም ተማሪዎች በ20 ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው ከጥቃቱ በፊት በእርሱ ቤት ውስጥ የልደት ድግስ ላይ ታድመው እንደነበር ተናግሯል።

“ቤታችንን ለቀው ከወጡ ከ5 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በበራችን በኩል የሚያልፍ ድምጽ የሚያሰማ እና መብራቱ ብልጭ ድርግም የሚል የፖሊስ መኪና አየን። የሆነ ችግር እንደተፈጠረ ገባን። ዘመዴ እና ጎደኞቹ እንደሆኑ ግን የምናውቀው ነገር አልነበረም” ብሏል።

ጥቃቱን በተመለከተ ቤተሰቦቻቸው የፍልስጤም ደጋፊ በሆነ አንድ ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅት አማካኝነት መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫቸዋውም “የሕግ አስከባሪ አካላት፣ የተሟላ ምርመራ እንዲያደርጉ እና ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ወንጀል አድርገው እንዲወስዱት እንጠይቃለን። ተኳሹ ለፍትህ እስኪቀርብ ድረስ ሰላም አይሰማንም” ብለዋል።

የአሜሪካ የእስልምና ምክር ቤት ጥቃት አድራሹን ለመያዝ የሚያስችል መረጃ ለሰጠ ሰው 10 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ከሁለት ወራት በፊት የእስራኤል እና ሐማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአሜሪካ ሙስሊም ጠል እና ፀረ ሴማዊነት ክስተቶች ተባብሰዋል። አካላዊ ጥቃት ማድረስን ጨምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጥላቻ ንግግር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ቀደም ሲል ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ዕጩ ቀርበው የነበሩት የቬርሞናንት የምክር ቤት አባሉ በርኒ ሳንደርስ ጥቃቱን አውግዘዋል።

በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ሦስት ፍልስጤማውያን እዚህ በርሊንግተን ቬርሞንት ውስጥ ለጥቃት መዳረጋቸው እጅግ የሚያስደነግጥ ነው ያሉ ሲሆን “ጥላቻ እዚህ ወይም ሌላ የትም ስፍራ ቦታ የለውም” ብለዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም ተልዕኮ አምባሳደር የሆኑት ሁሴን ዛምሎት በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው የሦስቱን ተማሪዎች ፎቶ ለጥፈው “ፍልስጤማውያን ላይ በጥላቻ የሚደረግ ወንጀል ሊቆም ይገባል” የሚል ጹሁፍ አስፍረዋል።