November 27, 2023 – Konjit Sitotaw
“ጦርነት ግጭቶችና መፈናቀሎች በግለሰብና ማህበረሰብ ላይ የሚፈጥሩት የአዕምሮ ቁስለት ከፍተኛ ነው” ዶ/ር ቢንያም ወርቁ
በሀገራችን የሚከሰቱ ጦርነት ግጭቶችና መፈናቀሎች በግለሰብ እንዲሁም በማህበረሰብ ላይ የሚፈጥሩት የአዕምሮ ቁስለት (Trauma) ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አእምሮ ህክምና ክፍል ውስጥ ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የአዕምሮ ቁስለት (Trauma) ሳይካትሪስት የሆኑት ዶ/ር ቢንያም ወርቁ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ቲክቫህ: ለመሆኑ የአእምሮ ቁስለት (Trauma) ምንድነው?
ዶ/ር ቢንያም፡ የአእምሮ ቁስለት ወይም በእንግሊዝኛው “Trauma” የሚባለው ቃል ከአዕምሮ ህመም ምድብ አንዱ ሲሆን በብዙኃኑ ህብረተሰብ ዘንድም የሚታወቅ ቃል ነው።
የአዕምሮ ቁስለት ሰዎች የሚገጥማቸውን ጥቃት ፣ ሰው ሰራሽም ሆነ ሰው ሰራሽ ያልሆነ አደጋና ከመደበኛው የሰው ልጅ ልምዶች ውጪ የሆኑ ከባድ አስጨናቂ ክስተቶችን ተከትሎ የሚፈጠር የአዕምሮ ህመም ነው።
ቲክቫህ፡ አንድ ሰው የአዕምሮ ቁስለት ደርሶበታል ተብሎ የሚገለፀው መች ነው?
ዶ/ር ቢንያም፡ አንድ ግለሰብ የአዕምሮ ቁስለት የሚያመጣ ጉዳት ደርሶበታል የሚባለው ከባድ አስጨናቂ ክስተት ሲደርስበት ነው። ግለሰቡ ሰው ሰራሽም ሆነ ሰው ሰራሽ ያልሆነ ለህይወቱ የሚያሰጋ ክስተት ሲደርስበትና አደጋው በሚደርስበት ጊዜ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሲሆን ግለሰቡ በቀጣዩ ጊዜ የአዕምሮ ቁስለት ሊደርስበት ይችላል ተብሎ ይታመናል።
ሁሉም ሰው አደጋ ሲደርስበት የአዕምሮ ቁስለት ይገጥመዋል ማለት ሳይሆን ለአዕምሮ ቁስለት የሚያጋልጡ አካላዊ ፆታዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃትን ጨምሮ ሰው ሰራሽ እና ሰው ሰራሽ ያልሆኑ አደጋዎች ግን አሉ።
ቲክቫህ፡ የአእምሮ ቁስለት ምልክቶች ምንድናቸው?
ዶ/ር ቢንያም፡ የአዕምሮ ቁስለት የተለያዩ ምልክቶች አሉት ከነዚህም መሃል በዋናነት፦
– Re experiencing ወይም የሃሳብ መሰንቀር ይህ ማለት የደረሰውን አደጋ ፣ ጥቃት ፣ ጉዳት በተመለከተ ሃሳብ ወይም ትውስታ እየተመላለሱ መምጣት ማለት ነው።
– ሽሽት፦ የደረሱብንን ነገሮች የሚያስታውሱ ነገሮች ሲመጡ መሸሽ ፤ ስለ አሰቃቂው ክስተት ላለማሰብ ወይም ላለመናገር መሞከር ክስተትቱን የሚያስታውሱ ቦታዎችን፣ እንቅስቃሴዎችን ወይም ሰዎችን ማስወገድ ሌላኛው ምልክት ነው።
– አዳጋው ተከትሎ አሉታዊ አስተሳሰብ እና ስሜት ማስተናገድና ተጠቂዎች የወደፊቱ ህይወቸው እንደጨለመ የማሰብና ተስፋ የማጣት ስሜት ሊኖራቸውና የመፍዘዝና፣ የስጋት፣ አንድ ቦታ ሳይረጉ ግራ ቀኙን መመልከትና ደኅንነት አለመሰማት አይነት ስሜት ሊኖራቸው ይችላል።
– መከፈል (dissociation) ማለትም ሰዎች ሰውነታቸው የራሳቸው እንዳልሆነ መቁጠር አካላቸው እያለ አዕምሮአቸው ሌላ ቦታ መጓዝ እንደ አንድ ምልክት ሆኖ ይቆጠራል።
ቲክቫህ፡ የአዕምሮ ቁስለት ማንን ሊያጠቃ ይችላል?
ዶ/ር ቢንያም፡ የአዕምሮ ቁስለት የትኛውም ሰው ላይ ሊደርስ ይችላል። ሆኖም በተለየ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ፣ ህፃናት ፣ አዛውንቶች ሲጠቀሱ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ለአዕምሮ ቁስለት ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
ቲክቫህ፡ ሰዎች በአዕምሮ ቁስለት ሲጠቁ ማድረግ ያለባቸው ምንድነው?
ዶ/ር ቢንያም፡ በአዕምሮ ቁስለት የተጠቁ ሰዎች የህክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው። ከዚህ ባሻገር ማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ባህላዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም የጓደኝነት፣ የመጠያየቅ፣ የአብሮነት እሴትን በመንተራስ እንደ ማኅበረሰብ የአዕምሮ ቁስለት ተጠቂ ሰዎችን በመደገፍና በማበረታታት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማድረግ ይቻላል።
