November 28, 2023 – Konjit Sitotaw 

“የአድአው ጥቁር አፈር፤ ተስፋዬ ገብረአብ ሕይወትና ምስጢር” የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፉ የተስፋዬን አወዛጋቢ ሕይወትና ምስጢራት ከቢሾፍቱ እስከ አስመራ በመጓዝ የሚተርክ መሆኑ ተገልጿል።

በጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ሽመልስ (ጉቺ) የተዘጋጀው “የአድአው ጥቁር አፈር፤ ተስፋዬ ገብረአብ ሕይወትና ምስጢር” መጽሐፍ የአነጋጋሪውን ጸሐፊ ቤተሰቦች፣ የቀድሞ ጋዜጠኞች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በማነጋገርና አያሌ ጥናጦችን በማካሄድ አመት ከሰባት ወር ገደማ ወስዶ የተዘጋጀ ነው።

ተስፋዬ ገብረአብ በኢትዮጵያ የሩብ ክፍለ ዘመን ታሪክ ውስጥ እጅጉን ሲያነጋግር የቆየ ደራሲ ሲሆን የሕይወት ታሪክ ዝግጅቱ ይህንን እንቆቅልሽ ለመፍታት ከኢትዮጵያ አንዳንድ አከባቢዎች እስከ ኤርትራ ድረስ ተጉዞ ጥናቶችን ማድረጉን የመጽሐፉ ደራሲ ተናግሯል።

“የአድአ ጥቁር አፈር፤ ተስፋዬ ገብረአብ ሕይወትና ምስጢር በ 18 ምዕራፎችና በ12 ንዑስ ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን 360 ገፆች አሉት። ተስፋዬ ገብረአብ ኢህአዴግን ከተቀላቀለ በኋላ በከፍተኛ ኃለፊነት ላይ ሆኖ በ”የቡርቃ ዝምታ” መጽሐፉ በኃላም የጋዜጠኛው፣ የደራሲውና የስደተኛው ማስታወሻ በሚሉ ሥራዎቹ ድጋፍና ተቃውሞ ሲያስተናግ ቆይቷል።

“የአድአው ጥቁር አፈር፤ ተስፋዬ ገብረአብ ሕይወትና ምስጢር” መጽሐፍ ”ደራሲና መንግስታዊ የሥራ ኃላፊው ተስፋዬ ገብረአብን ውስብስብ የሕይወት መልኮች ለመረዳት ሞክሯል።” ያለው የመጽሐፉ አዘጋጅ አብዛኛው አንባቢ የሚያነሳው ከተስፋዬ ድርሰቶች ጀርባ ያለው አከራካሪ ዓላማም ምንድነው የሚለው ጥያቄም ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጿል።