
( ሙሼ ሰሙ ) በውጭ ምንዛሪና በጥሬ እቃ እጥረት፤ በሰላምና መረጋጋት እጦት፣ በመንግስታዊ ተቋማት ሙስናና አገልግሎት ንፍገት የሚዘጉና በቋፍ የሚገኙ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱና የሚበተኑ ሰራተኞች ቁጥርም በአሳሳቢ ሁኔታ እያደገ መሆኑ በመገናኛ ብዙሃን በስፋት እየተዘገበ ነው።
በብረት፣ በመአድን፣ በቅባት እህል፣ በውኋና ለስላሳ መጠጥ፣ በቡና፣ በግንባታ፣ በሆቴልና ቱሪዝም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሚሰሩ የንግድ፣ የአገልግሎትና አምራች ድርጅቶች ስጋት፣ ፈተናና ዋይታ መፍትሔው ምንድን ነው? መንስኤው ከየት ነው? ጉዞውስ ወዴት ነው ? የሚል ድምጽ አለመስማቱ አሳሳቢ ነው ።
በየዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የስራ እድሎች መፍጠር የሚገባት ሀገር በብዙ ውጣ ውረድና ድካም የፈጠረቻቸውን ጥቂት የስራ እድሎች የማጣት ፈተና ሲጋረጥባት ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኖ ማነጋገሩ፣ ማወያየቱና መፍትሔ መሻቱ ትርፍ ነገር ሆኗል ወይስ እንደ ሀገር ተስፋ ቆርጠን ፈተናውን ለእድል ትተነዋል ?
ጉዳዩስ ከመንግስት አቅም በላይ ከሆነ እንደ ሕዝብ ምን እናድርግ? ተያይዘን እንውደቅ ወይስ እንተሳሰብ ? ለጊዜውም ቢሆን በቁና ከመዝረፍና ከማትረፍ እንዴት እንቆጠብ ? የትርፍ አዙሪት ውስጥ ገብተን መቋጫ በሌለው የዋጋ ንረትና የመሳሳብ ማዕበል ውስጥ እንጡዝ ወይስ ጊዜውን የዋጀ የግብይት ስርዓት እንዘርጋ።
ተያይዘን እንጥፋ ወይስ ፈተናውን በሞራል ከፍታ፣ በአስተውሎትና በመተሳስብ እንለፈው። ጊዚያዊ ቢመስልም የአሰተውሎት መፍትሔው በእያንዳንዳች እጅ ላይ ነው። ( ሙሼ ሰሙ )
