
በጐንደር የሚገኘው ዐቢየ እግዚእ ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም አስተማሪ የነበሩት እኒኽ መምህር፥ በሰው እጅ ተወግረው መገደላቸው ተሰምቷል። ጎንደር ዓቢየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ወቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያን የአቋቋም መምህር ፤ የታች ቤት ፣ የላይ ቤትና የሳንኳ አቋቋም ተጠያቂው ሊቅ መምህር ፍስሐ ዓለምነው ኅዳር 17 በግምት ከሌሊቱ 10:00 ገደማ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
መምህሩ በትላንትናው ዕለት ማታ መደበኛውን ትምህርት አስተምረው የሌሊቱን ትምህርት ለማስተማር ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚሄዱበት ሰዓት ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ተመትተው ወድቀው የተገኙ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕይወታቸውን ማትረፍ እንዳልተቻለ መምህር ፍሬ ስብሐት የቀድሞ የቤተክርስቲያኒቱ የአቋቋም መምህር ለተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ገልጸዋል።
ጸሎተ ፍትሐቱ ታላላቅ የጎንደር ሊቃውንት በተገኙበት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ሥርዓተ ቀብራቸው በትውልድ ሀገራቸው ጃንአሞራ እንደሚፈጸም ተገልጿል።
ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል በመምህር ፍስሐ ዓለምነው ዕረፍት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለውሉደ ያሬድ ሊቃውንት ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
መምህሩ፥ ሮጠው ማምለጥ የማይችሉ ዐይነ ስዉር ናቸው። ከዚኽ አንጻር እርሳቸውን የገደሉ ሰዎች ከድንጋይ ዘመን እንጂ ከአኹኑ ትውልድ አይቈጠሩም። እንዲያውም ራሳቸው ድንጋዮች ናቸው። በእርግጥ ሰውን መግደል የእኛ ዘመን ክፉ ባህል ቢኾንም፥ የአብነት መምህርን መውገር፥ ይልቁንም ራሱን ከአደጋ መከላከል የማይችል ዐይነ ስዉርን መግደል ግን የገዳዮችን ድንጋይነት ያመላክታል።የቤተ ክርስቲያን አምላክ፥ መምህሩን በቀኙ ያቁማቸው! ገዳዮቻቸውን ግን ይበቀላቸው!!
