November 28, 2023 – Konjit Sitotaw
የፈረንሳዩ የቴሌኮም ኩባንያ “ኦሬንጅ” ከኢትዮ ቴሌኮም የባለቤትነት ድርሻ የግዢ ጨረታ ሂደት ራሱን ማግለሉን ሰምቼያለኹ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
“ኦሬንጅ”፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የ45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለመያዝ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2021 ዓ፣ም ፍላጎቱን አሳይቶ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
ኾኖም “ኦሬንጅ” በጨረታው የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው በጽሁፍ እንደገለጠለት የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኩባንያው፣ ስትራቴጂውን በፍጥነት ለመተግበርም ኾነ እሴት የሚፈጥሩና የዕቅድ ማጠናቀቅን የሚፈቅዱ አስቻይ ኹኔታዎች የሉም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን እንደገለጠለትም ዘገባው አመልክቷል።
መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን የ40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለጨረታ ያቀርበው ከኹለት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ሲኾን፣ ኾኖም መንግሥት የጨረታ ሂደቱን አራዝሞ ሂደቱ እንደገና የተጀመረው ከዓመት በፊት ነበር።
