በትግራይ ከልል አድዋ ከተማ የሚገኘው የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከ13 ዓመታት በላይ በፋብሪካው ውስጥ በሠራተኛነት ማገልገላቸውን ለዋዜማ የተናገሩ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሠራተኛ፣ ከ30 ወራት በላይ ደመወዝ ባለማግኘታቸውና እስከ አኹን ወደ ሥራ ገበታቸው ባለመመለሳቸው ርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሠራተኞች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
የፋብሪካው የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር ገብረ ክርስቶስ በላይ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው ባኹኑ ወቅት ከ200 በማይበልጡ ሠራተኞች የጥገና ሥራዎችን እንደጀመረ ጠቅሰዋል። ሊቀመንበሩ፣ ወደ ሥራ ከተመለሱት ጥቂት ሠራተኞች መካከል አንዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሚከፈላቸው የደሞዛቸውን ሩብ ያህል እንደኾነ ጠቁመዋል።
ፋብሪካው ከ5 ሺ 200 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ ከ30 በላይ የሚኾኑት በምግብና መድኅኒት እጥረት ሕይወታቸው ማለፉንም ለዋዜማ ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ ደመወዝ እንዲከፈላቸው አስተዳደሩን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ ፋብሪካው ውድመት ስለደረሰበይ ደመወዝ መክፈል አንችልም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።
