November 28, 2023 

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ “ዋብር” በተባለች ተብላ የገጠር ከተማ ትናንት ምሽት 1:00 ሰዓት ገደማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

በድሮን ጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች በዚያው ምሽት በከተማዋ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ቀብራቸው መፈጸሙን ነዋሪዎቹ ለዋዜማ ገልጠዋል። ጥቃቱን ያደረሰችው ድሮን ከቀኑ 11:00 ሰዓት ጀምሮ ከተማዋን ስትቃኝ ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ታጣቂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በከተማዋ ባለፈው ጥቅምት ወር በተፈጸመ የድሮን እንደኾነ በተገመተ ጥቃት፣ ከ13 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዋዜማ በወቅቱ በሥፍራው ከነበሩ ነዋሪዎች አጣርታ መዘገቧ ይታወሳል።

በምሥራቅና በምዕራብ ጎጃም አንዳንድ አካባቢዎች፣ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት፣ አኹንም ድረስ የወረዳ ና የዞን ከተሞችን እንዲኹም ዞኖችን ከክልሉ መዲና ባሕርዳር ጋር የሚያገናኙ አንዳንድ የመኪና መንገዶች እንደተዘጉ መኾኑን ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጠዋል።