SPORTS ILLUSTRATED/INTERNET ARCHIVE

ከ 5 ሰአት በፊት

‘ስፖርት ኢሉስትሬትድ’ የተሰኘ እውቅ ስፖርት ላይ የሚያተኩር ድረ-ገጽ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ኤአይ የተዘጋጁ ጽሁፎችን ከሀሰተኛ የጸሐፊ ስም እና ምስል ጋር አትሟል የሚል ወቀሳ ከቀረበበት በኋላ ጽሑፎቹን አጥፋ።

አንድ የቴክኖሎጂ ተቋም የጽሑፎቹ አዘጋጆች ናቸው የተባሉ ሰዎች ምስልን ሰራሽ አስተውሎት ድረ-ገጽ ላይ ከተመለከተ በኋላ ጉዳዩን ሪፖርት አድርጓል።

በጉዳዩ የድረ-ገጹ ሰራተኞች መደናገጣቸውን የ ‘ስፖርት ኢሉስትሬትድ’ ሰራተኞች ማህበር ገልጿል።

አሳታሚ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ውስጣዊ ምርመራ እንደሚደረግ ገልጿል።

ስፖርት ኢሉሰትሬትድ መጽሄትና ድረ ገጽን የሚያስተዳድረው አሬና ግሩፕ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ነው የተባለው ጽሁፍ አድቮን ኮሜርስ በተባለ ሶስተኛ ወገን ትክክለኛ ነው ተብሎ እንዲታተም ፍቃድ ማግኘቱን ገልጿል።

ድርጅቱ ጨምሮም ጽሑፍ ብዙ ጥያቄዎች ስለተነሱበት ማስወገዱን ጠቅሷል።

አሬና ግሩፕ ከአድቮን ኮሜርስ ጋር ያለው ግንኙነት ያቋረጠ ሲሆን ይዘቱ ላይ ድርጅታዊ ምርመራ ያደርግበታል።

የስፖርት ኢሉስትሬትድ ማህብር “ይህ ድርጊት በጋዜጠኝነት ላይ ያለንን ሁሉንም እምነት የሚጥስ ነው” ካለ በኋላ “ደርጅቱ ከኮምፒውተር የሚመነጩ ጽሁፎችን ከማተም መቆጠብን ጨምሮ፣ ሁሉንም መሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርሆች እንዲያከብር እንጠይቃለን” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

አሬና ግሩፕ እንደሚለው ከሆነ አድቮን ኮሜርስ ሁሉንም ጽሁፎች ተመልክቶ በሰው የተጻፉና የአርትዎት ስራ የተሰራላቸው መሆናቸውን አረጋግጧል።

ጨምሮ ይህ ለሶስተኛ ወገን የምንሰጠው ኃላፊነት ጽሁፍ ከሌላ ያልተወሰደ ወይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ አለመሆኑን እንዲረጋገጥልን ነው ብሏል።

ሆኖም ኩባንያው የሰራተኞቹን ደኅንነት ለመጠበቅ አንዳንድ ጽሃፊዎች የብዕር ስም እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል።

በዚህም ምክንያት የጸሀፊው ፎቶ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ እንዲሁም ስሙ ኢንተርኔት ላይ የማይገኝ ሊሆን ይችላል ብሏል።

ይህ ክስተት ሰው ሰራሽ አስትውሎት ጋዜጠኞችን በቀላሉ ሊተካና ሃሰተኛ መረጃን ሊያሰራጭ ይችላል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጓል።

ሚች ጎዲች የስፖርት ኢሉስትሬትድ ኤድተርና የማህበሩ መሪ ሲሆን መጽሄቱ ያተመው ጽሁፍ የሰዎች ልፋት መና የሚያስቀር ነው ብሏል።