” እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ? በረሃብ ማለቅ አለብን ? ” – ተፈናቃዮች
ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በ2015 ዓ/ም በነበረው ማንነት ተኮር ግጭት የተነሳ ቤት እና ንብረታቸውን ጥለው ወደ አማራ ክልል፤ ቻግኒ የመጡ ተፈናቃዮች እርዳታ እየተደረገልን አይደለም፤ በረሃብ ምክንያት ባለፉት ሁለት ሳምንታት 2 ህፃናት ህይወታቸው አልፏል ብለዋል።
በቻግኒ የሚገኙት 2000 የሚደርሱ ተፈናቃይ ወገኖች ሲሆኑ በግለሰብ ፍርስራሽ ቤቶች እና ጅምር ፎቆች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።
የተፈናቃዮቹ አስተባባሪ አቶ መሀመድ ሀሰን፦
” ካለፈው ሳምንት ብቻ ሁለት ህፃናት በረሃብ ምክንያት ሞተውብናል።
እኛ እስከ ዞን እስከ ክልል ድረስ ወስደን ደብዳቤ አስገብተናል። ዞኑ እራሱ ፈርሞ የሞቱትን ሰዎች ዝርዝር በዛ ላይ አልተጠቀሱም ግን እንደሞቱ ሪፖርት አድርገናል።
በረሃብ ምክንያት ህፃን 34፣ ትላልቅ ሰዎች 21 በአጠቃላይ 55 ሰዎች እንደሞቱብን ሪፖርት አድርገናል።
እኛ ሰው ጠግቦ ይደር እያልን አይደለም ያለነው ቢያንስ ቀምሶ ይደር ህይወት ይዳን ነው። ምናለ መንግስት እንኳን ባያግዘን ሌላ ድርጅቶች ገባ ብለው ቢያግዙን ይሄ ሁሉ ጉዳት ይሄ ሁሉ ህዝብ እንዴት በረሃብ ይሞትብናል ?
ሰዎች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሄድ ብለው የቀን ስራ ሰርተው እንዳበላ ያልታደሰ መታወቂያ ይዛችሁ አትሄዱም ተብለን ተዘግቶብናል። ተንቀሳቅሰን የቀን ስራ ካልሰራን እንዴት አድርገን ነው ህይወታችንን ማቆየት የምንችለው ? መንግሥትም እያገዘን አይደለም።
መንግሥት በቅርብ ወደሀገራችሁ ትገባላችሁ የሚል ነገር አንስቷል። ይሄም ቢሆን ደስ ይለናል በተለያዩ ቦታዎችም ምዝገባ አለ የሚባል ነገር አለ እዚህ ዞን ግን እስካሁን የመጣም ሆነ የተጠየቅነው ነገር የለም።
ወይ እርዳታ አልተደረገ፣ ወይ ወደተፈናቀልንበት ቦታ መንግስት ያለውን ነገር አረጋግጦ እየመለሰን አይደለም፣ እንዴት ነው የምንሆነው ኢትዮጵያዊ አይደለንም እኛ በረሃብ ማለቅ አለብን ? ”
ከተፈናቃዮች መካከል አንዲት 60 ዓመት እናት፤ ” እመጫትም ወልዳ የምትበላው የምትቀምሰው አጥታ ቁጭ ብለናል። እየተሰቃየች ነው ያለችው ተቸግረን ነው ያለነው በጣም በጣም ተሰቃይተናል ” ብለዋል።
በምስራቅ ወለጋ ለ52 ዓመታት እንደኖሩ የሚናገሩት የ75 ዓመት እድሜ ያላቸው አዛውንት አቶ ሀሰን መሀመድ ከ8 ልጆቻቸው 5 ወንድ ልጆቻቸው በግጭቱ እንደተገደሉና አሁን ላይ ከቀሪ 3 ሴት ልጆቻቸው ጋር በቻግኒ የግለሰብ ፍርስራሽ ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሚላስ የሚቀመስ የለንም የሚሉት አዛውንቱ ” በጣም አጣዳፊ የሆነብን የምግብ ጉዳይ ነው፤ ልጆችን እየቀብርን ነው በረሃብ ምክንያት መንግስት ሊሰማን አልቻለም አላወቀንም እንዳንል አንድ ጊዜ እርዳታ መጥቶልናል፤ ስማችንም በኮምፒዩተር ገብቶ ይታወቃል። መጠለያ አልተሰጠንም የትም ተበትነን በየከተማው በየበረዳው ተቀምጠን ነው በደል የደረሰብን ብርዱ ፀሀዩ ረሃቡ እየተፈራረቀብን ነው ” ብለዋል።
የቻግኒ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ፅ/ቤት ተወካይ ባለሞያ አቶ የሱፍ ሁሴን ምን አሉ ?
– ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ነው እርዳታ የመጣው። አንዴ ተሰጣቸው ቆመ እስካሁን የለም።
– በረሃብ ተጎድተው ታመው የተኙ ሰዎች አሉ፣ በቂ ህክምና እንዳያገኙ ብር የላቸውም።
– ሃምሳ አምስት ሰው እንደሞተባቸው ለኛ ሪፖርት ሰጥተውናል። እሱን ደግሞ ለዞን ለክልል በደብዳቤ አሳውቀናል። ኮሚቴም ሄዶ እንዲያነጋግር ተደርጓል።
– ክልሉ ‘እርዳታ አለ ግን ለማድረስ የመንገድ የፀጥታ ሁኔታ ችግር በመሆኑ ማድረስ አልችልም’ የሚል ነው።
ያንብቡ ፡ https://telegra.ph/VOA-11-29 VOA
