November 29, 2023 

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ከ 36 በላይ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸው ተገለጸ !

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ በሕገ ወጥ ታጣቂ ኃይሎች ባለፉት 3 ቀናት ብቻ በደረሰ ጥቃት ከ 36 በላይ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸው ተገልጿል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን መረጃ ያደረሱት ተጎጂዎች እንደገለጹት ከሆነ በሶሌ መድኃኔዓለም እና ሴሮ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 13 ቀን በተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ 28 ኦርቶዶክሳዊን መገደላቸው በመጠቆም ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ 8 ምእመናን በድምሩ 36 ምእመናን መገደላቸው ጠቅሰዋል፡፡ በርካቶችም ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቁሟል፡፡

በሽርካ ወረዳ በተደጋጋሚ ጊዜ በደረሰው ጥቃት ነፍሰጡር ሴትን ጨምሮ ጨቅላ ሕጻናት የተገደሉ ሲሆን የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።

በአካባቢው ምእመናን ላይ እንዲህ ዓይነት መሰል ጥቃት ሲፈጸም በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ በ 2016 ዓ.ም ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ጥቃቱ የደረሰባቸው ምእመናን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በአካባቢው እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ለሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት ሀገረ ስብከቱ የማሳወቅ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል ።