Skip to content

‹‹የተሻለ ዕርዳታ ለማግኘት የተጎጂዎችን ቁጥር የሚያጋንኑ ክልሎች አሉ›› የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

ድርቅ በተከሰተባቸው በተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች ዕርዳታ ሲቀበሉ
ማኅበራዊ‹‹የተሻለ ዕርዳታ ለማግኘት የተጎጂዎችን ቁጥር የሚያጋንኑ ክልሎች አሉ›› የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር…ተመስገን ተጋፋው

ቀን:

November 29, 2023

በአገር አቀፍ ደረጃ በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ትኩረት እንዲያገኙና የተሻለ ድጋፍ እንዲኖራቸው፣ ክልሎች የተጎጂዎችን ቁጥር በማጋነን እንደሚያቀርቡ የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው ክልሎች ትኩረት ለማግኘትና የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ይህንን ያህል ሰዎች ሞተውብኛል፣ ይህንን ያህል ተጎድተውብኛል የሚል መረጃ እንደሚያመጡ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አታለል አቡሃይ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡በዚህ መሠረት እስካሁን ሁሉም ክልሎች ይህንን ያህል ሰዎች ሞተውብኛል ብለው ለኮሚሽኑ ሪፖርት አለማቅረባቸውን የገለጹት ባለሙያው፣ የቅድሚያ ቅድሚያ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልገናል ብለው ለላኩ ክልሎች ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ዕርዳታ መስጠት ካቆሙበት ጊዜ ጀምሮ፣ መንግሥት በራሱ አቅም ያለውን ክምችት በመጠቀም አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ክልሎች ማሠራጨቱን አስታውሰዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 7.3 ሚሊዮን ሰዎች የቅድሚያ ቅድሚያ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፣ እስካሁንም ለእነዚህ ሰዎች በሁለት ዙሮች የምግብና የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አብራርተዋል፡፡እስካሁን በአጠቃላይ 799 ሺሕ ኩንታል እህል በሁለት ዙሮች እንዲደርሳቸው የተደረገ መሆኑን፣ 1.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ በየአካባቢው እህል ገዝተው ማግኘት ይችላሉ ተብለው ለተለዩ ሰዎች በጥሬ ገንዘብ መሰጠቱን አክለዋል፡፡ዕርዳታ ሰጪ ተቋማት ካቋረጡበት ጊዜ ጀምሮ 7.9 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ግብዓቶች ድጋፍ መደረጉን፣ መንግሥት በሦስተኛ ዙር ድጋፍ ለማድረግ በቂ የሆነ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በአማራ ክልል ለ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድርቅ የተጎዱ መሆናቸውንና በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ፣ ማዕከላዊና ደቡብ ምሥራቅ ዞኖች የሚገኙ 981 ሺሕ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ትልቅ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በአፋር ክልል ዞን አንድ፣ ዞን ሁለት፣ ዞን ሦስት፣ ዞን አራትና ዞን አምስት የሚገኙ 225 ሺሕ ሰዎች ለከፍተኛ ረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውንና በአጠቃላይ 7.3 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹ ጠቁመዋል፡፡በድርቅ፣ በጎርፍና በሌሎች ችግሮች የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያገኙ የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ መንግሥት የሚከተለውን አሠራር ተከትለው ከሠሩ አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡በተለያዩ ጊዜያት ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር ተከታታይ ስብሰባ ሲያደርግ፣ ይህንን ያህል ሰዎች ሞተውብኛል በማለት ያነሳ ክልል እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተው በማስረዳት ብዙ ጊዜ ጉዳዩን ለሌላ አጀንዳ ይጠቀሙበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Share this:

  • Share on Telegram (Opens in new window) Telegram
  • Share on WhatsApp (Opens in new window) WhatsApp
  • Tweet

Like this:

Like Loading…

Your true media source

All rights reserved

%d