
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ የእስራኤል ወታደሮች በፈጸሙት ጥቃት ሁለት ህጻናትን ጨምሮ አራት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የፍልስጤም ባለስልጣናት ተናገሩ።
የደህንነት ካሜራ ቪዲዮዎች የስምንት ዓመቱ አደም አል-ጉል እና የ14 ዓመቱ ባዝል አቡ አል-ዋፋ በጄኒን ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ በጥይት ሲመቱ አሳይተዋል።
የእስራኤል ጦር ተጠርጣሪዎች ፈንጂዎችን ወታደሮች ላይ በመወርወራቸው የተኩስ ምላሽ መስጠታቸውን አስታውቋል።
ጦሩ በጥቃቱ “ሁለት ከፍተኛ አሸባሪዎች” መገደላቸውንም ገልጿል።
በጋዛ ሰርጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በዌስት ባንክ ከፍተኛ አለመረጋጋት አለ።

በደህንነት ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ እንደሚያሳየው አንድ ታዳጊ ዞር ብሎ መሮጥ እንደጀመረ በፍጥነት መሬት ላይ ሲወድቅ ያሳያል። ይህ ታዳጊ የስምንት ዓመቱ አደም አል ጉል ሲሆን በጥይት ተመትቶም ነው የወደቀው። አንድ ጓደኛውም አስከሬኑን ከጎዳናው ወደ ጥግ ሲጎትተውም በቪዲዮው ላይ ይታያል። የእስራኤል ወታደሮች በጄኒን የተፈናቃዮች የመጠለያ ስፍራ የከፈቱትን ጥቃት ጨርሰው ሲወጡም ነው አደም ጭንቅላቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ያለፈው።
በአቅራቢያው ደግሞ ደግሞ የ14 ዓመቱ ጓደኛው ባዝል አቡ አል-ዋፋ በጥይት ደረቱ ላይ ከተመታ በኋላ ህይወቱን ለማዳን ሲፍጨረጨር ነበር። የወደቀበት አካባቢ በተኩስ እሩምታ ሲታመስ ነበር።
በጄኒን ሆስፒታል ሲደርሱ ሁለቱም ታዳጊዎች ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።
የእስራኤል መከላከያ ጦር ባወጣው መግለጫ “በጄኒን ካምፕ በተደረገ ዘመቻ በርካታ ተጠርጣሪዎች ፈንጂዎችን ወደ ጦሩ ወርውረዋል” ብሏል።
በምላሹም ወታደሮቹ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተኩስ ምላሽ እንደሰጡም ገልጿል።
የባዝል አስከሬን በተጨናነቀው የሆስፒታሉ የሬሳ ክፍል ውስጥ ለቀብር ሲዘጋጅ የታዳጊው አስከሬን በሐማስ አረንጓዴ ሰንደቅ ዓላማ ሲጠቀለል አንድ ዘመድ ተመልክቷል። ይህ ባዝል የሚፈልገው ነገር አልነበረም ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“እሱ ንጹህ ነው። ከታጣቂዎቹ ወገንም አይደለም። በትምህርት ቤቱ ጎበዝ፣ ጥሩ ልጅ እና ደግ ነበር” ሲል በንዴት እና በሃዘን መካከል ሆኖ ተናግሯል።
የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ዊሳም ባከር የልጆቹ በጥይት ጭንቅላታቸውን እና ደረታቸውን መመታታቸው ሆን ተብሎ ኢላማ ተደርገው መገደላቸውን ያሳያል ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት በጄኒን ይህ ነው የሚባል ከጥቃት የሚያስጥል ቦታ የለም” ብለዋል።
በጋዛ ያለው ጦርነት በዌስት ባንክ ያለውን ውጥረት ጨምሮታል። የእስራኤል ጦር በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ወረራዎችን ይፈጽማል።
ጦሩ በጄኒን ባደረገው ወረራ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ከፍተኛ አዛዥ የሆነው መሃመድ ዙበይዲ እና ዊሳም ሃኖን የተባለ አብሮት በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነበረ ግለሰብ መግደሉን ተናግሯል።
ዙበይዲን በግንቦት ወር አንድ እስራኤላዊ በተገደለበት እና በርካታ ወታደሮች በቆሰሉበት ሁለት ጥቃቶች ተሳታፊ ነበር ሲል ጦሩ ከሷል።
ልክ እንደ ሐማስ ሁሉ በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች ምዕራባውያን አገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ሁለት የአካባቢው አዛዦቹ መገደላቸውን አረጋግጧል።
የእስራኤል ጦር ባደረገው ወረራ 17 ተፈላጊ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ገልጿል።

የእስራኤል ሚሳኤሎች፣ የእጅ ቦምቦች እና ፈንጂዎች በጄኒን የተፈናቃዮች መጠለያ ባደረሱት ጥቃት ከፍተኛ የጥፋት ጠባሳ አሳርፈዋል። በርካታ ቤቶች ወድመዋል ወይም ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው ሊሆን ይችላል ተብለው የሚታመኑ ሰዎችን ለመፈለግ ጥረት እያደረጉ ነበር።
በዚህ ዒላማ የተደረጉት የታጣቂ መሪዎች እንደሆኑ እስራኤል ብታሳውቅም የስምንት እና የ14 ዓመት ልጆችም አብረው ተገድለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከመስከረም 26 ወዲህ በዌስት ባንክ ቢያንስ ከ50 በላይ ህጻናትን ጨምሮ 225 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን ተናግሯል።
