November 30, 2023 

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሀብሩ-መርሣ ወረዳ ጋቲራ ደብረ ፀሐይ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሣሪያ ተደብድቦ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. ምሽት ፲፩ ሠዓት የሠርክ ጉባኤ ትምህርት ላይ እያሉ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ዘጠኝ ካህናትና ፀበልተኞች መቁሰላቸውን የወረዳ ቤተክህነቱ ገልጧል።

በትምህርታዊ ጉባኤ ላይ እያሉ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽረ ግቢ፣ በቤተልሔሙና በፀበልተኛ መጠለያ ቤቶች በርካታ ከባድ መሣሪያ ያረፈ ሲኾን በደብሩ አስተዳዳሪ፣ ሰባኬ ወንጌልና በፀበልተኛ ሕሙማን ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሐብሩ-መርሣ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ታዴዎስ ይመር እንደገለፁት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በውርጌሣ ጤና ጣቢያ መታከማቸውንና ፫ ሰዎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ደሴ እና ወልድያ ሪፈራል ሆስፒታሎች መላካቸውን ገልፀዋል።

የከባድ መሣሪያ ተኩሱ በአካባቢው ዛሬም መቀጠሉን የገለፁት ዋና ጸሐፊው የአብነት ተማሪዎችና ለፀበል የመጡ ሕሙማን ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ተበትነዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ጋዞ ወረዳ ቤተክህነት ብር አፋፍ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ጥቃት ሦስት ካህናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት