
30 ህዳር 2023, 14:31 EAT
በዘመናዊው ዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ዲፕሎማቶች መካከል ቀዳሚው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሄንሪ ኪሲንጀር በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ውስጥ ጉል ሚና ነበራቸው።
አንዳንዶች እንዲያውም የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት መሃንዲስ የሚባሉት ኪሲንጀር ከ50 ዓመታት በፊት አሜሪካ ከአፍሪካ ብሎም ከኢትዮጵያ አንጻር የቀረጹት ፖሊሲ አሁን ድረስ በአሜሪካ አቋም ላይ እየተንጸባረቀ ነው ብለው ያምናሉ።
በናዚ አስተዳደር በአይሁዶች ላይ ሲፈጽም የነበረውን ጭቆና በመሸሽ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከጀርመን ወደ አሜሪካ የተሰደዱት ሄንሪ አልፍሬድ ኪሲንጀር ወደ አሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ወደ ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ከመድረሳቸው በተጨማሪ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ስመ ጥር ለመሆን ችለዋል።
ኪሲንጀር የአሜሪካ ዲፕሎማት፣ የፖለቲካ ሳይንቲስት፣ የፖለቲካ አማካሪ የነበሩ ሲሆን፣ በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ዘመን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እንዲሁም የፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ኪሲንጀር በሚከተሉት የውጭ ፖሊሲ “እውናዊነትን” እንደሚከተሉ ይነገርላቸዋል በዚህም ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመቀበል እንደየ አግባቡ መሥራት ምርጫቸው ነው ይባላሉ።
በተለይ የቀዝቃዘው ጦርነት ከፍተኛ ውጥረት ላይ በደረሰበት ጊዜ አሜሪካ ከምሥራቁ የኮሚኒስት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከፍጥጫ እንዲወጣ እና በውይይት ላይ እንዲመሠረት ሠርተዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥም በአስራኤል እና በአረቦች መካከል ሰላም እንዲወርድ ጉልህ ሚና ነበራቸው።
- የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄንሪ ኪሲንጀር በ100 ዓመታቸው አረፉ30 ህዳር 2023
- የአሜሪካ ባሕር ኃይል የእስራኤላዊያንን መርከብ አግተው የነበሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ28 ህዳር 2023
- ሐማስ ከእስራኤል አፍንጫ ስር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ እንዴት ኃይሉን መገንባት ቻለ?29 ህዳር 2023
በዚህም ከፍተኛ ውዝግብን ያስነሳ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በተቀበሉ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሽልማቱ ለጦር ወንጀለኛ የተሰጠ ነው በማለት ውግዘት ደርሶባቸዋል።
ኪሲንጀር በአፍሪካ፣ በደቡብ እና መካከለኛው አሜሪካ ውስጥ ከተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥታት፣ ግጭቶች እና የመብት ጥሰቶች ጋር ስማቸው በአሉታዊ ሁኔታ ይነሳ ነበር።
ጉምቱው ዲፕሎማት እንደሚሉት የትኛውም አገር ብሔራዊ ጥቅሙን ለማስከበር ያስችለኛል ብሎ የሚያስበውን መንገድ እና አማራጭ ያለምንም ይሉኝታ እና የሞራል ጥያቄ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብለው ያስባሉ።
ከዚህ አኳያም ኪሲንጀር በአንድ ወቅት ሲናገሩ “በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ የሞራላዊ ትክክለኛነትን የሚያስቀድም አገር፣ ትክክል የመሆንም ሆነ የራሱን ደኅንነት ማስከበር አይችልም” ሲሉ ከሁሉ በላይ ብሔራዊ ጥቅም ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነ አመልከተዋል።
ተቺዎቻቸው ኪሲንጀር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ለአሜሪካ ጥቅም ለማስገኘት ሲሉ የሌሎች ጉዳት እና ደም መፋሰስ ግድ የማይሰጣቸው ጨካኝ አድርገው አሁን ድረስ ይወቅሷቸዋል።
ከዚህ አኳያም ቺሊ ውስጥ ግራ ዘመሙን መንግሥት ለመገልበጥ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥት ግልጽ ባለሆነ ሁኔታ በመደገፍ እና ‘ቆሻሻው ጦርነት’ በመባል የሚታወቀው የአርጀንቲና ጦር ሠራዊት በሕዝቡ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ ‘እንዳላየ’ በመሆን ይከሰሳሉ።
የኪሲንጀር ደጋፊዎች ዲፕሎማቱን “ተጨባጭ ፖለቲካን የሚያራምዱ” እያሉ ሲያሞካሿቸው፣ ነቃፊዎቻቸው ደግሞ ድርጊታቸውን “ኢሞራላዊ” በማለት ይወቅሷቸዋል።
በአንድ መቶ ዓመት እድሜያቸው ያረፉት ኪሲንጀር ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የሚነገር ታሪክ አላቸው።

ኢትዮጵያ፣ አሜሪካ እና ኪሲንጀር
ከአራት አስርት ዓመታት በፊት አንስቶ በአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ውስጥ ዋነኛው ሰው የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር፣ የምሥራቁ ሶሻሊስት እንቅስቃሴ በአፍሪካ በተለይም ነጻ የወጡ አገራት ውስጥ የመስፋፋት አዝማሚያ ያሳይ በነበረበት ጊዜ እና በኢትዮጵያም የአብዮት እንቅስቃሴ ሲካሄድ ሁኔታውን በቅርበት ይከታተሉ ነበር።
የዐፄ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ዘመን መጠናቀቂያ አካባቢ ላይም ኢትዮጵያን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት ሊይዘው የሚገባው አቋም እና የሚከተለውን ፖሊሲ በተመለከተ ምክር ይሰጡ ነበር።
ሄንሪ ኪሲንጀር የአሜሪካንን የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በሚመሩበት በአውሮፓውያኑ 1972 በወቅቱ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋን በሚመለከት ‘ምሥጢራዊ’ ሪፖርት አዘጋጅተው ማቅረባቸውን በኢትዮጵያ ላይ የጻፉት አሜሪካዊው ተመራማሪ ቴዎዶር ቬስቴል በመጽሃፋቸው ላይ አስፍረዋል።
በዚህ ሰነድም ላይ ኪሲንጀር “አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ውጥረቶችን እና የጎሳ፣ የሃይማኖት እና ሌሎች ልዩነቶችን ጨምሮ ሌሎች ደካማ ጎኖችን መጠቀም እንደሚያስፈልጋት” ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመሥረቱ በኩል ጉልህ ሚና የነበራት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በርካታ የአህጉሪቱ አገራትም ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት እየወጡ የነበረበት ጊዜ ነበር። በዚህም ሳቢያ የፓን-አፍሪካ እንቅስቃሴ እየጎለበተ መጥቶ ነበር።
አሜሪካ ደግሞ የአውሮፓ ወዳጆቿ ጥቅም በአፍሪካ ውስጥ እንዲከበር እና በቀይ ባሕር አካባቢ ያለትን ቦታ ለማስጠበቅ ካላት ፍላጎት የተነሳ የፓን-አፍሪካ እንቅስቃሴዎችን እና የለውጥ ፍላጎቶችን በበጎ አትመለከታቸውም ነበር።
ሄንሪ ኪሲንጀር የፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በነበሩበት ወቅት፣ ኒክሰን ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴን በዋይት ሐውስ ውስጥ ሲያገኟቸው ኪሲንጀር “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ አገራት የቅርብ ወዳጃችን ናት” ብለው ነበር።
ኪሲንጀር በወቅቱ ኃይለ ሥላሴን “ለዘብተኛ የምዕራባዊያን ደጋፊ እና በአፍሪካ ጉዳዮች ቀንደኛ ሚና መጫወት የሚችሉ” ሲሉ ለፕሬዝዳንት ኒክሰን በላኩት ማስታወሻ ገልጠዋል።
ኪሲንጀር ከብሔራዊ ደኅንነት አማካሪነት አልፈው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከንጉሣዊው አስተዳዳር ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ተሻገረች፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነትም ተቀሰቀሰ፣ አልፎም ፊቷን ከካፒታሊስቱ ወደ ኮሚዩኒስቱ ዓለም አዞረች።
ኃይለሥላሴ ወደ አሜሪካ አቅንተው ኒክሰንን ባገኙበት ወቅት ኪሲንጀር ባጠናቀሩት ፅሑፍ ንጉሡ በአገር ቤት እና ከአገር ውጭ የተለያዩ ተቃውሞዎች እየገጠሟቸው እንደሆነ አስፍረው ነበር።
በለተይ ደግሞ የንጉሡ ትልቁ ጭንቀት ሆነው የኤርትራ ነፃነት ግንባር እንቅስቃሴ እንደሆነ ኪሲንጀር ለፕሬዝዳንቱ በፃፉት ወረቀት ላይ አስፍረዋል።
አሜሪካ በኒክሰን ዘመነ-መንግሥትም ሆነ በፎርድ አስተዳዳር ትከተለው የነበረው “ትዊን ፒላር” የተሰኘው ፖሊሲ “ትክክል አልነበረም” ብለው የሚከራከሩት ፖለቲካል ሳይንቲስቱ አዮዋኒስ ማንዚኮስ ናቸው።
ምሑሩ አሜሪካን ዲፕሎማሲ በተሰኘው ድረ-ገፅ ላይ አሜሪካ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ላይ ታራምድ የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚል ፅሁፍ ለንባብ አብቅተዋል።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የ25 ዓመታት የመከላከያ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 1953 የገባቸው ምሥራቃ አፍሪካዊቷ አገር በቀጣናው ቁልፍ ሚና አላት ብላ በማሰብ ነበር።
ኃይለ ሥላሴ በመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዘመናቸው ከፕሬዝዳንት ኒክሰን ጋር ያላቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ባይቋረጥም፣ እየሻከረ መጥቶ እንደነበር ይነገራል።
ሁለቱ አገራት በገቡት ስምምነት መሠረት አሜሪካ ለኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንድታደርግ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውን ቃኘው የጦር ጣቢያን አሜሪካ መጠቀሟን እንድትቀጥል ተግባብተው ነበር።
ነገር ግን አሜሪካ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለኤርትራ የተሻለ ነፃነት ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች ለውጦችን እንዲያደርግ ትሻ ነበር።
አዮዋኒስ፤ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ተወግደው ደርግ ወንበር ሲይዝ ሄንሪ ኪሲንጀር የአሜሪካ ፖሊሲ ወዲያውኑ እንዲቀየር አልፈለጉም ነበር ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1976 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር ኢትዮጵያ በኤርትራ ነፃነት ጉዳይ የምታራምደውን ፖሊሲ መልሳ ካላጤነች የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠው እርዳታ አደጋ ውስጥ ይወድቃል ሲሉ ዝተው ነበር።
ኪሲንጀር፤ ደርግ ፊቱን ወደ ኮሚዩኒስቱ ዓለም ሙሉ በሙሉ አያዞርም ብለው ያመኑባቸው ምክንያቶች ነበሩ።
አንደኛው ምክንያት ለምዕራባዊያን ቀና አስተሳሰብ አላቸው የሚባሉት ጄኔራል አማን አንዶም የደርግ ባለሥልጣን ሆነው መሾማቸው ነው። የአማን አንዶም ሹመት ለኤርትራ የትግል ጥያቄ አንድ መልስ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ጥሎ ነበር።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የደርግ እንቅስቃሴ ርቆ መሄድ የማይችል እንቅስቃሴ ነው ብሎ ማመኑ ነበር።
አሜሪካ ደርግን በተመለከተ የነበራት አስተሳሰብ የተዛባ ነበር የሚሉት ምሑሩ፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ኅብረት ሲያዞሩ ነው ይህ እውን የሆነው ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1977 ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ-መሐላ በፈፀሙ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ መሪ ሆኑ።
ሚያዚያ 1977 ላይ አሜሪካ የቃኘው ጣቢያ መዘጋቱን እና በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል የተገባው ስምምነት ማብቃቱን አሳወቀች።
ከዚህ በኋላ ነው የመንግሥቱ ኃይላማርያም መንግሥት ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ሶቪየት ያዞረው፤ አሜሪካ ደግሞ ወደ ሶማሊያ በመዞር ወታደራዊ እርዳታ ማድረግ የጀመረችው።