
የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣዉ ረቂቅ መመሪያ ክፍል አራት አንቀፅ 15 ተራ ቁጥር 5 መሠረት “አንድ ተማሪ በወሊድ ምክንያት 15 ተከታታይ የትምህርት ቀናት ካረፈች በኃላ ትምህርቷን መቀጠል ትችላለች፤ ሆኖም ግን 16 ቀናትና ከዚያ በላይ ከትምህርት ገበታዋ ከቀረች ከዘመኑ ዓመት ትምህርት ትታገዳለች።” የሚል ረቂቅ መመሪያ ማዉጣቱ ይታወሳል።
ይህንንም በተመለከተ በዛሬዉ ዕለት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴትች ማህበር ይህንን መግለጫ በማህበሩ ቅጥር ግቢ ዉስጥ ሰጥቷል።
ይህም የሆነዉ ተቋሙ በሆቴሎች ሊሰጥ የታሰበዉ መግለጫ በማን እንደሆነ ባልታወቀ መልኩ በመከልከሉ መሆኑንም ሰምተናል።
መንግስት ይህንን ረቂቅ መመሪያዉን እስኪቀይረዉ ድረስ ሰላማዊ የዉትወታ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የፕሮግራም ማናጀር ቤተልሄም ደጉ ለጣብያችን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስቴርም መመሪያዉ ረቂቅ መሆኑን በመግለፅ፣ ተቀራርበዉ እንዲሰሩ እንደጠየቃቸዉም ጨምረዉ ተናግረዋል።
ለትምህርት ሚኒስቴር፣ለህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትና ለመላዉ ህብረተሰብ ክፍልም ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል።
ጥሪዉንም ካስተላፉት ድርጅቶች መካከልም የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ሴቶች ይችላሉና ሌሎች ሰባት ድርጅቶች መመሪያውን ተቃዉመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብትንየሚገድብ ረቂቅ ሕግ አውጥቷል።
ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን አወንታዊ የድርጊት ድንጋጌዎች የሚንድ ብቻ ሳይሆን የሴቶችን መሠረታዊ የመማር መብቶችም በግልጽ የሚነፍግ ነዉ ሲሉም ፕሮግራም ማናጀሯ ቤተልሄም ደጉ ተናግዋል።
ይህንን ዓይነት መመሪያዎቸን ሁሉም የሚመለከተዉ ጉዳይ መሆኑን በማመን ድርጊቱን ሊቃወም ይገባል ብለዋል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አቋሙን እንደገና እንዲያጤነውም ማህበሩ ጠይቋል።
