አንቶኒ ብሊንከን ከእስራኤሉ ባለስልጣን ጋር

1 ታህሳስ 2023, 08:16 EAT

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤል በጋዛ ከሐማስ ጋር በምታደርገው ጦርነት ለሲቪሎች ጥበቃ የምታደርግበትን መለኪያዎችን በግልጽ አስቀምጠዋል።

ከእስካሁኑ በጣም ጠንካራ በተባለው የአሜሪካ አስተያየት፤ የእስራኤል መንግሥት ተጨማሪ ፍልስጤማውያንን ማፈናቀል እንዲያቆም፣ እንደ ሆስፒታሎች፣ የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ እና የውሃ ተቋማት ባሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ብሊንከን መናገራቸው ታውቋል።

አሜሪካን ወደ እርምጃ የሚያስገቧትን ቀይ መስመሮችን ከማስቀመጥም ወደ ኋላ አለሉም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መልዕክቱን ለማድረስ ወደ እስራኤል ተጉዘዋል። ይህ ጉዟቸው ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ አራተኛው ነው።

የአሁኑ ጉብኝት በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በተደረሰው ስምምነት የተኩስ አቁም ፋታው በቆመበት ወቅት የተደረገ ነው።

እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን ለመቀጠል ማቀዷን የተቀበሉት ብሊንከን “በሰሜን ጋዛ ያየነው ከፍተኛ የዜጎች ህይወት እና መፈናቀል በደቡብ እንዳይደገም አሜሪካ ትፈልጋለች” ሲሉ አስምረውበታል።

ሐማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሲህ 200 ሰዎችን ሲገድል 240 የሚሆኑት ደግሞ አግቷል። ከዚያን ወዲህ እስራኤል በወሰደችው የማያባራ የአጸፋ ጥቃት 6 ሺህ የሚደርሱ ህጻናትን ጨምሮ ከ14 ሺህ 800 በላይ ፍልስጤማውያንን ገድላለች ሲል በጋዛ የሚገኘውና በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን በመምታት ጭምር ሰሜናዊውን ጋዛን ወደ ፍርስራሽነት ቀይሯታል።

ውድመቱ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን አስተዳደር አካሄድ ቀይሮታል። ከጥቃቱ በኋላ ለእስራኤል የማያሻማ ድጋፍ ሲሰጥ ነበረው አስተዳደር አሁን ለሲቪሎች ጥበቃ ትኩረቱን ወደ ማሳደግ እና በጋዛ ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታዎችን በማቃለል ላይ አድርጓል።

አስተዳደሩ ያሳየው የዘገየ ለውጥ በወዳጅ አረብ አጋሮች ዘንድ ቁጣ እና ከአስተዳደሩ ውስጥ ደግሞ በባይደን ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

ተጨማሪ የፍልስጤማውያን መፈናቀል “ከማንኛውም የሰብአዊ ድጋፍ አቅም በላይ ነው” ብለዋል አንድ ከፍተኛ ኃላፊ።

መጀመሪያ ላይ በእስራኤል መንግሥት በቀረበው መሠረት ሠላማዊ ዞኖች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መገልገያዎች እና መጠለያዎች አቅራቢያ ባሉ በርካታ ቦታዎች መተግበር እንደሚያስፈልጋቸውም አብራርተዋል።

ብሊንከን ወደ ጋዛ የሚደረገውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ዕድል መኖር እንዳለበትም አስምረውበታል።

ለወታደራዊ ዘመቻው የጊዜ ገደብ ይቀመጣል ወይ የሚለውን ጥያቄ ከመመለስ ታቅበው፤ እስራኤል በአሜሪካ አካሄድ እንደምትስማማ ብቻ ተናግረዋል።

እስራኤል በሐማስ የተፈጠረውን ስጋት ለማስወገድ ያላትን ግብ ዋሽንግተን እንደምትደግፍ እና የፍልስጤም ታጣቂዎች በሲቪል ህዝብ መካከል ሲደበቁ ዘመቻው ውስብስብ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለጦርነቱ ግብዓት የሆነውን አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ከፍተኛ ወታደራዊ እርዳታ ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ አስተዳደሩ የመጨረሻውን አቅሙን ለመጠቀም ዝግጁ አለመሆኑን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስታውቋል።

ከብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን ጋር በደርዘን የሚቆጠሩ ዴሞክራት ሴናተሮች ባደረጉት ስብሰባ የእስራኤል የጦር መሣሪያ አጠቃቀም የአሜሪካንን ሕግ ያከብራል ወይ ብለው ሲጠይቁ የተነገራቸውም ይሄው ነው።

ይልቁንስ ትኩረት የተሰጠው ፕሬዚዳንት ባይደን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በግል ገፋፍተው ተጽኖአቸውን እንዲጠቀሙበት ነበር።

ቀጣዩ የጦርነት ምዕራፍ እስራኤል መልዕክቱን ምን ያህል እንደደረሳት የሚያሳይ ይሆናል።