December 1, 2023 – Konjit Sitotaw 

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር በጦርነት መፍታት አይቻልም ስንል ለጠ/ሚኒስትር አብይ ነግረናቸዋል ሲሉ ማይክ ሀመር ተናገሩ ።

የአሜሪካ የታችኛው ምክር ቤት ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ ‘’በኢትዮጵያ ተስፋ ወይንስ ስጋት፣ የአሜሪካ ፖሊሲ ሁኔታ’’ በሚል ርዕስ ትላንት ሐሙስ ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚመለከታቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናትን ጠርቶ ምስክርነት ሰምቷል።

የኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴ በነበረው ፕሮግራም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር እና የዩኤስኤድ የአፍሪካ ረዳት አስተዳደር ቴለር ቤከልማን ተገኝተው ገለጸ የሰጡ ሲሆን ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽም ሰጥተዋል።

የኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጆን ጄምስ  በትግራይ ተካሂዶ የነበረው ጦርነት በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች ላይ በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀይባህር ዙሪያ የወደብ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ንግግርን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል።

በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌደራል መንግስት ወታደሮች መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የአሜሪካ መንግስት እየጣረ ነውን ተብለው የተጠየቁት ማይክ ሃመር አወን የሚል ምላሽ ሰጥተው ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከጠ/ሚኒስትሩ እና ከከፍተኛ አማካሪዎቻቸው ጋር በተገናኘንበት ወቅት በአማራ ክልል ያለውን ችግር በወታደራዊ መንገድ ምንም አይነት መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ገልጸንላቸዋል፣ ሰላማዊ ድርድር እንዲጀምሩ መክረናቸዋል ብለዋል።