በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች የታጠቁ ኃይሎች ሰሞኑን ፈጽመዋቸዋል በተባሉ ጥቃቶች 36 ሰዎች መገደላቸውን ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች። ኅዳር 13 ምሽት ሶሌ በተባለ ቀበሌ 17 ሰዎች ባንድ ላይ የተገደሉ ሲኾን፣ በጢዮ ለቡ ቀበሌ በዚያው ዕለት ምሽት 11 ሰዎች መገደላቸውንም ምንጮች ገልጸዋል። ኅዳር 17 ቀን ደሞ፣ በኮኔ ቀበሌ ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደተገደሉ ዋዜማ ተረድታለች። በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል አንዲት ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ፣ ጨቅላ ሕጻናት፣ አረጋዊያንና ሴቶች ይገኙበታል ተብሏል። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የሽርካ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ተስፋዬ በየነ፣ በአስተዳዳሪነት ከተሾሙ አንድ ሳምንት ብቻ እንደኾናቸው በመግለጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ጊዳሚ ከተማ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ዘጠኝ ምዕመናንን ባለፈው ዓርብ ሌሊት አፍነው ወስደው እንደገደሏቸው መስማቱን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በምዕመናኑ ላይ ግድያውን የፈጸመውን ታጣቂ ቡድን ማንነት ገና እንዳላወቀች የቤተክርስቲያኗ ሃላፊዎች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የቤተክርስቲያኗ ሃላፊዎች መንግሥት በጸሎት ላይ በነበሩ ምዕመናኗ ላይ በተፈጸመው ግድያው ላይ ምርመራ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ዜና ምንጩ ጨምሮ አመልክቷል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን፣ በምዕመናኑ ላይ ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያወጣችው ይፋዊ መግለጫ የለም። ( ዋዜማ )